
ምርጫ 97 - ያመለጠ የዴሞክራሲ ግንባታ ዕድል
ይህ የጽሁፍ አበርክቶ በምርጫ 1997 ወቅት የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ብሎም የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰብ ያበረከቱት ነው። ጸሃፊያችን ሃሳባቸውን እንጂ ማንነታቸውን እንድናጋራ ፈቃዳቸውን አልሰጡንም።የጥላሁን ገሰሰን “ከሰው ሰው ይለያል” የተሰኘውን ሙዚቃ ከጀርባ እያዳመጡ ፅሁፉን ያነቡ ዘንድ ፀሃፊያችን በጠየቁት መሰረት እኛም በግራ በኩል ባለችው ምልክት ላይ ሙዚቃውን አያይዘንዋል። ከ20 ዓመታት በፊት በግንቦት ሰባት ቀን 1997 ዓ.ም የተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የተከናወነበት ሂደት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስኬታማ የነበረ መሆኑን በርካታ ምርጫውን የታዘቡ እንደ የካርተር ሴንተር፤ የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ያሉ ተቋማት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በምርጫው ተቃዋሚ ድርጅቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ የተሳተፉ ሲሆን፣ በፓርላማ ውስጥ ያላቸውን መቀመጫ ከማሳደጋቸውም በላይ (ከ12 ወደ 170 ወንበር) የአዲስ አበባ ምርጫን ሙሉ ለሙሉ አሸንፈዋል። የሆነ ሆኖ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ጥርጣሬ በኅብረተሰቡ ውስጥ ውጥረት እንዲሰፍን ተደርጎ በሰኔ ወር 1997 ከፍተኛ አመጽ ተቀሰቀሰ። ለዴሞክራሲ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ የተጣለበት የምርጫ ሂደት በሚያስቆጭ ሁኔታ ተጨናገፈ።በዚህ አጭር ጽሑፍ ተስፋ ተጥሎበት ስለነበረው ምርጫ 97 እና የወቅቱ ድባብ፤ የምርጫውን ሂደትና ፈንጥቆ ስለነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል መዳፈን ለመግለጽ እሞክራለሁ።የወቅቱ የምርጫ ሂደትበበርካታ ሀገራት የሚካሄዱ ምርጫዎች በሦስት ምዕራፎች ያልፋሉ። በመጀመሪያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የራሳቸውን ዝግጅት አድርገው ፕሮግራማቸውን በማስተዋወቅና ሕዝብ ውስጥ በመንቀሳቀስ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት እንዲሁም እርስ በእርሳቸው ክርክር የሚያደርጉበት ነው። ሁለተኛው ምዕራፍ ድምጽ የሚሰጥበት፤ ቆጠራ የሚካሄድበትና ውጤት የሚገለጽበት ምዕራፍ ሲሆን፣ ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ በድምጽ ቆጠራው መሰረት አሸናፊ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች በውጤቱ መሰረት መንግሥት ለመመስረት የሚረከቡበት ነው።የምርጫ ዝግጅትና ቅስቀሳ“ምርጫ 97 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ካካሄዳችው ሁለት ምርጫዎች (1987 እና 1992) ለምን የተለየ ሆነ?” የሚለውን ጥያቄ ልዳስ። ይህን ጥያቄ ማንሳቱና ማብራራቱ ምናልባትም በምርጫ 97 ወቅት የነበረውን ኹኔታ ለመገንዘብ ይጠቅማል ብዬ አምናለኹ።እንዲኸ ነው፡- በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ሀገሪቱን ባስተዳደረበት የመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት (1983 እስከ 1993 ዓ.ም) የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተዋሉ ነበር። ከዚያም ባሻገር የኤርትራ መንግሥት ወረራን ለመመከት የተካሄደው ጦርነት እንዲሁም 14 ሚሊዮን ሕዝብን ለአደጋ ያጋለጠው ድርቅ መንግሥትን ከፍተኛ ችግር ውስጥ አስገብቶት ነበር። በዚህም የተነሳ በኅብረተሰቡ ውስጥ በተለይም በከተሞች ብሶትና ተስፋ መቁረጥ የተስፋፋበት ግዜ ነበር።ኢሕአዴግ፥ እነዚህን ችግሮች በቶሎ ለመፍታትና ልማትን ለማሳለጥ የትጥቅ ትግል በሚያካሂድበት ወቅት ይከተለው የነበረውን የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን ተወ። እናም የካፒታሊስት ስርዐት የሚገነባ መሆኑን በመግለጽ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ንድፈ ሐሳብን መሰረት ያደረጉ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። በዚህ ወቅት አዳዲሶቹን ፖሊሲዎች ለመተግበር ከፍተኛ መከራ የገጠመው ቢሆንም፣ ችግሮችን በመፍታት ልማትን ለማሳለጥ ሌት ከቀን መሥራት ጀመረ። በምርጫ 97 ዝግጅት ወቅትና ምርጫው በሚካሄድበት ጊዜም በሀገሪቱ (በገጠርም ሆነ በከተማ) እዚህ ግባ የሚባል የሕዝብን ኑሮ የለወጠ ልማት አልነበረም። ለምሳሌ በገጠር በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጥ የታየ ሲሆን በከተሞች በተለይ በአዲስ አባባ ደግሞ የአነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች፤ የቤቶች ልማት እንደዚሁም ሰፋፊ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች የተጀመሩበት ጊዜ ነበር።ይህ በእንዲህ እያለ፣ ኢሕአዴግ ምርጫ የሕዝብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ በመሆኑ በ1997 የሚካሄደው ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ መሆን ይገባዋል የሚል አቋም ይዞ ተንቀሳቀሰ። ድርጅቱ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የሕዝብን መብት ለማክበር የቆመ ድርጅት በመሆኑም፣ ይህ አቋም ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ1983 ዓ.ም ደርግን አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን ሲይዝ፣ ለብቻው ሳይሆን በርካታ ድርጅቶችን አሳትፎ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሲደረግ ነበር።በመሰረቱ አንድ ሕዝብ በምርጫ ተጠቃሚ የሚሆነውና ሉዐላዊነቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማረጋገጥ የሚችለው የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለት ይበጀኛል ያለውን በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው። በሕገ-መንግሥቱ ላይ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብቶች እንደሚከበሩ ተደንግጓል፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት በመገንዘብ ወደ ምርጫ ውድድር የገባው፥ ቢሸነፍም ውጤቱን በጸጋ መቀበል የዴሞክራሲ መርህ መሆኑን በመገንዘብም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ተቃዋሚዎች በብዙኀን መገናኛ ሰፊ እድል እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲ ምርጫ ማስፈጸሚያ መንገድ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር የፖሊሲ ክርክር እንዲካሄድ አደረገ። ክርክሩም ምርጫው ከመካሄዱ ከ9 ወር በፊት (ከመስከረም 1997) ጀምሮ ተካሄደ። ከዚህም በላይ የምርጫ ሕጉ እንዲሻሻል ተቃዋሚ ድርጅት የሆነው አዴፖ/መድሕን ያቀረበውን ጥያቄ በመመርመር የምርጫ ሥርዓቱ ከአብላጫ ድምጽ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲቀየር ከተጠየቀው በስተቀር ለአብዛኞቹ ጥያቄዎች ይሁንታን ሰጠ። በተጨማሪም ኢሕአዴግ የምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ጥረት ያደረገው ተቃዋሚዎች መድረክ አጣን በሚል ምክንያት ሊያስነሱ የሚችሉትን ሕዝባዊ አመጽ ለመግታት ነበር፡፡የኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች የምርጫ ክርክርእንደ ኢሕአዴግ ሁሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም በምርጫው ለመሳተፍ የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርገዋል። ለምሳሌ “ስንበታተን የምርጫ ድምጹም ይከፋፈላል” በሚል እሳቤ ብዙዎቹ አንድነትን ፈጥረው ተንቀሳቅሰውም ነበር። በዚህም መሰረት በራሳቸው በተቃዋሚዎች በመካከል ብሎም ከኢሕአዴግ ለዘጠኝ ወራት የዘለቀ ሰፊ እና የተጋጋለ ክርክር ለመካሄድ በቃ። ሕዝቡም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክርክሮቹን በመከታተል የሚስማማውን ለመምረጥ ዕድል አገኝቶ ነበር።የፖለቲካ ክርክሩን መድረክ ያዘጋጁት በዋናነት እንደ ኢንተር-አፍሪካ የመሳሰሉ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተካሄዱ ክርክሮችም ነበሩ። ለክርክሮቹ መነሻም በኢሕአዴግ በኩል ፖሊሲዎቹ የሆኑት የመሰረተ ልማት፣ የገጠር፣ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት፣ የመሬት ፖሊሲ፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ፋይዳ፣ ስለፌዴራሊዝምና የብሔር እኩልነት ወዘተ ናቸው። ብዙዎቹ ኢሕአዴግን በመወከል የተሳተፉ ተከራካሪዎች አቀራረባቸው በተገቢው ሁኔታ ያልተዘጋጁ በሚመስል መልኩ ነበር። ይህን ሁኔታ የታዘቡት አንዳንድ ግለሰቦች ስለሁኔታው ሲገልጹ “ኢሕአዴግ በባህሪው ሠርቶ በማሳየት እንጂ ስለሥራው ብዙም የሚናገር አይደለም” ይሉ ነበር፡፡ እውነትም በድርጅቱ ‘ሥራችን ይናገራል፣ እኛ ስለሥራችን ብዙም መናገር የለብንም’ የሚለው አስተሳሰብ በየጊዜው የሚንጸባረቅ መሆኑን እኔም እገንዘባለሁ። በጊዜው ኢኮኖሚው ከውድቀት ተነስቶ ማንሰራራት መጀመሩም ሆነ አስተማማኝ ሰላም ስለመኖሩ በምርጫው ክርክሮች በግልጽ አልቀረበም፡፡ ከምርጫው ሁለት ዓመት በፊት የተገኙትን መልካም ውጤቶች እንኳን በጥልቀት ለማስረዳት በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ ከማቅረብ ይልቅ ጥልቀት በሌለው ሁኔታ ሥራዎቹን አስተዋወቀ፡፡ በተቃዋሚዎችም በኩል ምርጫ ቢያሸንፉና የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙ ስለሚከተሉት የልማት አቅጣጫ እዚህ ግባ የሚባል ፖሊሲና ስትራቴጂ አልቀረበም፡፡ከዚህም በላይ ተቃዋሚዎች የመንግሥት ፖሊሲዎችን እያጥላሉ የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት ይጥሩ ነበር። ለምሳሌ ከላይ እንደገለጥኹት፥ በከተሞች ኢሕአዴግ የልማት ሥራዎችን የጀመረው ዘግይቶ ስለነበር በርካታ ሥራ አጦች ነበሩ። ተቃዋሚ ድርጅቶችም የሥራ አጦችን ብሶት ማራገብ ከመጀመራቸውም በላይ፣ ለበርካታ ሚሊዮን ሕዝቦች የትምህርት እድል የፈጠረላቸውን ትምህርት ማጥላላትን ተያያዙት። ተማሪዎችንም ተስፋ ለማስቆረጥ ‘ተምራችሁ የት ትደርሳላችኹ’ የሚል ዘመቻ አካሄዱ። በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ትምህርት “ትውልድ ገዳይ ነው” በሚል ከመፈረጃቸውም በላይ፥ “ተምረኽ የት ትደርሳለኽ!“ “የተቸገረ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” የሚሉ ከባባድ መልእክቶችን በመጠቀም ወጣቱ ‘ተምረን የት ልንደርስ?!’ በሚል ተስፋ ማስቆረጥን ተያያዙት።በተጨማሪም የሕዝብን ብሶት በማባባስ ለማሳመጽ የባለሥልጣናትን ስም እያነሱ ‘እገሌ ይሄን ያህል ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውጭ አስቀምጧል/ እገሊትም ይህን ያህል ፓውንድ አስቀምጣለች’ በሚል የፈጠራ ወሬ ወጣቱን የአመጽ መሣሪያ እንዲሆን ገፋፉት። ኢሕአዴግም የተቃዋሚዎቹን አፍራሽ ቅስቀሳ ተከታትሎ በአግባቡ ከማክሸፍ ይልቅ ተቃዋሚዎች በከተሞች የተንሰራፋውን ሥራ አጥ ኃይል ተጠቅመው ወደ ሥልጣን ለመምጣት እየተረባረቡ ነው በሚል እሳቤ፥ ሥራ አጥ ወጣቶችን “አደገኛ ቦዘኔ” በማለት የተቃዋሚዎቹ ማኅበራዊ መሰረት ናቸው የሚል አንድምታ አስተላለፈ። “አደገኛ ቦዘኔ” የሚለው አጠራር በመሰረቱ ትክክል አልነበረም። ምክንያቱም ወጣቶቹ ሥራ አጦች እንጂ ሥራ ጠል አልነበሩምና። ይህ አባባልም ወጣቶቹ መንግሥት “አደገኛ ቦዘኔ” ብሎ ሊያጠፋን ነው ብለው በማሰብ ወደ ተቃዋሚዎች አስተሳስብ እንዲያዘነብሉና በሥርዓቱ ላይ የማመጽን አስፈላጊነት እንዲቀበሉ ያደረገ ይመስለኛል፡፡የምረጡኝ ቅስቀሳየምርጫ ቅስቀሳው የተካሄደው በሚዲያ በሚተላለፉ መልዕክቶች ብቻ አልነበረም። የኢሕአዴግ ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች በየምርጫ ክልላቸውና ወረዳቸው እየተገኙ የምረጡኝ ቅስቀሳ ከማከናወናቸውም በላይ፥ ከተቃዋሚዎችም ጋር በየጣቢያው የምርጫ ክርክር ያደርጉ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች (በተለምዶ ፒክ አፕ፣ አይሱዙ ተብለው በሚጠሩት) እየተጫኑና የድምጽ ማጉሊያ በመጠቀም፤ አልፎም ትልልቅ ሰላማዊ ሰልፎች በማካሄድ በተለይም በከተሞች የምረጡኝ ቅስቅሳ ይካሄድ ነበር። ሕዝቡም በሬድዮና ቴሌቭዥን የሚካሂዱትን ክርክሮች ያደምጥና ይመለከት፣ አልፎም በወቅቱ እንደአሽን ፈልተው የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚያወጧቸውን ጽሑፎች ይከታተል ነበር።አንዳንድ ጊዜ ከአዲስ አባባ ውጭ በመኪና ስንሄድ ትንንሽ ልጆች በየመንገዱ ቆመው የቅንጅትን የምርጫ መወዳደሪያ ሁለት ጣት (V) ምልክት በትንንሽ ጣቶቻቸው እያወጡ ያሳዩን ነበር። የ97 ምርጫ የፓለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን የመላ ሕዝቡን (በገጠርም በከተማም የሚገኘውን) ቀልብ የሳበ ነበር። ለዚህም ማስረጃ በሚያዝያ ወር የመጨረሻው ቅዳሜ በኢሕአዴግ፥ እንዲሁም በማግስቱ እሁድ በቅንጅት የተካሄዱትን መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎችን መጥቀስ ይቻላል።የድምጽ መስጠትና ውጤትበምርጫው ዕለት ግንቦት 7 በመላው ኢትዮጵያ ሕዝቡ በሌሊት ተነስቶ እስከ ማታ ድረስ ድምጽ ሰጠ። የድምጽ አሰጣጡ ሂደት በጣም ሰላማዊ ሆኖ አለፈ። የሆኖ ሆኖ የምርጫ ሂደቱ ገና ሳይጠናቀቅና ቆጠራ ሳይካሄድ የመኢአድ ፓርቲ መሪ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል በሚያስገርም ሁኔታ ፓርቲያቸው ምርጫውን እንዳሸነፈና ኢሕአዴግም ምርጫውን እንዳጭበረበረ መግለጫ ሰጡ።የድምጽ መስጠት ሂደቱ እንደተጠናቀቀም፣ በወቅቱ የነበሩት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ገለጹ። አያይዘውም፥ የተፈጠረው ውጥረት እንዲበርድ፣ መራጩም የምርጫውን ውጤት በጥሞና እንዲጠብቅና እንዲቀበል እንዲሁም ግጭትን ለማስቀረት በማሰብ መንግሥት ለአንድ ወር ለሚሆን ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ እንደከለከለ አስታወቁ።የድምጽ ቆጠራው እንዳለቀ በውጤቱ፥ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ እንደተሸነፈ፣ በፌዴራል ደረጃ በርከት ያሉ ወንበሮችን ያጣ ቢሆንም ለፓርላማው ግን አብላጫውን ድምጽ መያዙ ተገለጸ። ተቃዋሚዎች ደግሞ በ1992 ከነበራቸው 12 የፓርላማ ወንበር በ97 ምርጫ ወደ 170 ወንበር አሳደጉ። የሆነ ሆኖ ተቃዋሚዎች ሙሉ በሙሉ ምርጫውን ባለማሸነፋቸው የምርጫውን ውጤት ላለመቀበል ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል መነሻ አመጽ ማነሳሳት ጀመሩ።አመጽ የማነሳሳት ድርጊቶችቅንጅቶች መሸነፋቸውን ባለመቀበልና በማንኛውም መንገድ ሥልጣን መያዝ ይገባናል በሚል ብሂል፥ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ሰበብ በተከታታይ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት አመጽ የመቀስቀስ እንቅስቃሴ ጀመሩ። በሀገሪቱ ምርጫ ሕግ በምርጫ ውጤቱ ያልተስማማ ወገን በመጀመሪያ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄዶ እንዲያመለክት፤ በምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ካልተስማማ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ተቀምጧል። አንድ ዴሞክራሲንና ሕግን የሚያከብር ድርጅት ይህንን ሕጋዊ መንገድ የሚከተል ቢሆንም፤ የቅንጅት አመራር ግን አግባብ ያለውን መንገድ መከተል አልፈለገም። ምክንያታቸውም ምርጫ ቦርዱም ሆነ ፍርድ ቤቱ ለኢሕአዴግ ያዳላል የሚል ነበር።በዚህም ምክንያት የጎዳና አመጽ ተቀስቅሶ ግርግሩ ሲባባስ ፖሊስ አድመኛውን ለመበተን ብሎ በተኮሰው ጥይት የአንዲት ወጣት ሕይወት በሚያሳዝንና ባልተገባ ሁኔታ አለፈ። ይህ በመሆኑ በመጸጸትና ሌላ ሕይወት እንዳይጠፋ ሁኔታውን የሚያበርድ እርምጃ በመውሰድ ፈንታ፣ የቅንጅቱ አመራሮች የወጣቷን ሞት ለጎዳና ነውጥ እንደማቀጣጠያ ቤንዚን ተጠቀሙበት። በመሆኑም የጎዳና ነውጡ የመንግሥት ንብረት በማውደም፤ አንበሳ አውቶብስን በድንጋይ በመደብደብ፤ የመንግሥትና የግል ተሽከርካሪዎችን በማቃጠል፤ በየመንገዱ አሮጌ ጎማዎችን በማቃጠልና መንገድ ላይ ድንጋይ እየከመሩ መንገዶችን በመዝጋት ተቀጣጠለ፡፡ፖሊስም እንደ ማርያም ጠላት ተወስዶ የድንጋይ ናዳ ወረደበት፤ ጥይት ተተኮሰበት። ለምሳሌ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ ጸጥታ ለማስከበር በኦራል ተጭነው ሲሄዱ በነበሩ ፖሊሶች ላይ ቦንብ ተወርውሮባቸው ጥቂቶቹ ሲሞቱ በርካታዎቹ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባችው ነበር፡፡ ፖሊሶችም አድማውን ለመበተንና ሁኔታውን ለማረጋጋት በተኮሱት ጥይት በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ። የሆነ ሆኖ ግርግሩ በሦስተኛው ቀን (ሰኔ 3) ሰከነ።በተቃዋሚዎች “እኛ ሁሉንም ጠቅልለን ካላሸነፍን ምርጫው ዴሞክራሲያዊ አይደለም” የሚል ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት የተነሳ በርካታ ወጣቶች ያለአግባብ ሕይወታችው ጠፋ። ወላጆችንም ጧሪ ቀባሪ አሳጧቸው፡፡ እዚህ ላይ ‘ኢሕአዴግስ ለምን ወደ ጥይት ሮጠ?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ መነሳቱም ተገቢ ይመስለኛል።በመሰረቱ ኢሕአዴግ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የወሰዳቸውን እርምጃዎችና ብሎም ሽንፈት ቢመጣ እንኳን ሥልጣኑ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን ከላይ ገልጫለኹ፡፡ የሆነ ሆኖ ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት በጸጋ ባይቀበሉት እንኳ፣ ከላይ በገለጽኩት ደረጃ የመንገድ አመጽ ያስነሱ ይሆናል በሚል ዝግጅት በማድረግ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገው ኢሕአዴግም ይህንኑ ተጠቅሞ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ነበረበት (እኔም ተማሪ ሆኜ በንጉሡ ዘመን ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ስንረብሽ አብዛኛውን ጊዜ የሚበትኑን በአስለቃሽ ጢስና በፖሊስ ቆመጥ ነበር)። የሰኔው የጎዳና ነውጥ እንዳይደገም የምርጫ ውዝግብ የሚፈታበትን መንገድ አና ስልት በዓለም አቀፍ የምርጫ አማካሪ ድርጅት በኩል እንዲዘጋጅ ተደረገ። ኢሕአዴግ የምርጫ ሂደቱን አስመልክቶ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታዎች ለማስተናገድ ስልቱን ለሁሉም ፓርቲዎች በማቅረብ ሁሉም የተስማሙበት የቅሬታ አፈታት ስልት ተዋቀረ። የተመሰረተው ስልትም ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥሩ መንገድ እንደነበር የምርጫ ታዛቢዎች፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የመሰከሩለት ነበር፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የችግር መፍቻ መንገድ በወቅቱ በነበረው ውጥረት ውስጥ ሊሠራ ስለማይችል፣ አዲስና ሁሉም ፓርቲዎች የተስማሙበት አሰራር ተዘጋጀ፡፡ በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎች በሰጡት የጽሑፍ ሪፖርት (በሪፖርቱ ገጽ 4 እና 5 ላይ ይገኛል) ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ቅሬታዎች በደካማ ማስረጃ (poor evidence) የተገለባበጠ ምስክርነትና ደካማ መከራከሪያ (week argument) ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።በተቃራኒው ግን አብዛኛው ኢሕአዴግ ያቀረባቸው ቅሬታዎች በማስረጃ የተደገፉ ከመሆናቸውም በላይ ወኪሎቻቸውና ምስክሮቻቸው በደንብ የተዘጋጁ እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በመሆኑም ድርጅቱ አብዛኛውን ቅሬታ ያቀረበበትን ማሸነፉ እንደማያስደንቅ አስታውቋል።ለማጠቃለል፥ የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎች ከዚህ የሚከተሉትን 4 ነጥቦች አስቀምጠዋል።የቅሬታ ሰሚ ሜካኒዝሙ ለነበረው ውጥረት ያየለበት ሁኔታ ጥሩ እንደነበር፣የቅሬታ አገማገሙም የተቀመጠውን ሂደት (ፕሮሲጀር) የተከተለ እንደነበር፣ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለቅሬታዎቻቸው ጠቃሚ ማስረጃ (Substantial evidence) ለማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን ምስክሮቻቸው የማይጣጣሙ (Inconsistent) እንደነበሩ፣ኢሕአዴግ ግን ጉዳዩን (Case) በደንብ ማቅረቡና መከራከሩ።በተጨማሪም የድርጅቱ አጠቃላይ ግምገማ የምርጫ ሂደቱ (polling process) አወንታዊ (positive) ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለግምገማቸው የሰጡት ነጥብ 64% የሚሆኑት ጉዳዮች (cases) ጥሩ ናቸው ሲሉ፥ 24% ደግም በጣም ጥሩ በሚል አስቀምጠዋል፡፡ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ አሸናፊ በተባለበት በርካታ የምርጫ ጣቢያ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ቅሬታ አቀረቡ፡፡ ኢሕአዴግም እንደዚሁ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ቅሬታ አቀረበ፤ ቅሬታ የቀረበባቸው ጉዳዮች ከተመረመሩ በኋላ በ31 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ ከፍተኛ ክፍተቶች (serious irregularities) መኖሩ ታወቀ። ከቀረቡት 31 ቅሬታዎች 17 በኢሕአዴግ፣ 7 በተቃዋሚዎች፣ 4 በኢሕአዴግና በአንዱ ወይም በሌላው ተቃዋሚ ድርጅት ጋር ቅንጅትንም ጨምሮ በጋራ የቀረበበት ነው። ቀሪው 3 ደግሞ በምርጫ ቦርድ ውጤቶች ያልተወሰና ዳግም ነበሩ።ቅሬታዎቹ ከተመረመሩ በኋላ ኢሕአዴግ ያቀረባቸውን 17 ቅሬታዎች ሲያሸንፍ፣ ተቃዋሚዎች ያቀረቧቸው 7 ቅሬታዎችን በሚመለከት ደግሞ ኢሕአዴግ ተሸንፏል። 4ቱ በጋራ የቀረቡት ቅሬታዎችም በጋራ ያቀረቡት ድርጅቶች እንደዚሁ አሸንፈዋል።ዳግም ምርጫ የተካሄዱባቸው ጣቢያዎች ከ29 ሺህ 438 ውስጥ 575 ሲሆኑ፣ ከመቶ ሲሰላ ከሁለት በመቶ (2%) ያነሱ ነበሩ። የምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳየውም አብዛኛዎቹ ጥፋተኞች (culprit) ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢሆኑም ኢሕአዴግም ከደሙ ንጹህ አልነበረም። የዳግም የጎዳና ነውጥ መከሰትከላይ እንዳነሳኹት፥ የምርጫ ሂደቱን የማጣራትና ቅሬታን የማስተናገድ ሂደት በፓርቲዎች ስምምነት መሠረት ተካሂዷል። በተጨማሪም አመጹን ለማስቀረት መንግሥት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም ከቅንጅትና ኅብረት አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይትና ድርድር አካሂዷል። ሆኖም የጎዳና ላይ ነውጥን ማስቀረት አልተቻለም።ቅንጅት የተጣራውን የምርጫ ውጤትና ያሸነፈውን መቀመጫ በመያዝ ወደ ፓርላማ እንደመግባት ፋንታ፣ በየክፍለ ከተማው የመረጠውን ሕዝብ እየሰበሰበ “ወደ ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ?” የሚል አስቂኝ ጥያቄ በማንሳት “ፍቃድ” ጠየቀ። በመጨረሻም በአመጽ ሥልጣን ለመያዝ የሚያልሙት መሪዎች ሁሉንም መቀመጫ ካላሸነፍን በሚል ስሜት ሁለተኛውን የጎዳና ላይ ነውጥ በጥቅምት ወር 1998 ውስጥ ቀሰቀሱ። እንደ መጀመሪያው ሁሉ በድጋሚ ክቡር የሆነው የፖሊሶችና ጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ በርካታ የሰው ሕይወት ጠፋ፣ ንብረትም ወደመ። ነውጡ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን መንግሥት ለነውጡ ቅድሚያ የሚሰጡት የቅንጅት መሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ወሰነ። በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ሕብረት እና ኦፌዲን እንዲሁም ኢዴፓ (ከቅንጅት ራሱን በመነጠል) ፓርላማ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን በማለት አቋማቸውን አሳወቁ።በነገራችን ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እነ ኢዴፖ ወደ ፓርላማ መግባታቸው ለፓርላማው ሕይወት ሰጥቶት ነበር። ምክንያቱም በፓርላማ ውስጥ ለውሳኔ የሚቀርቡ ጉዳዮች ሁሉ በለሆሳስ የሚያልፉበት ተቋም መሆኑ ቀርቶ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር የሚካሄድበት መድረክ ሆነ። በተለይም ጠቀላይ ሚኒስትር መለስ በየሁለት ወሩ ወደ ፓርላማው መጥተው የአባላቱን ጥያቄ በሚመልሱበት ወቅት የሚካሄዱት ውይይቶችና ክርክሮች በጣም አስተማሪ ነበሩ።የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሂደት ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲ የሚነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እንዲሁም የሚሰጡ መልሶች አስተማሪ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዴም አስቂኝ ስለነበሩ፥ እኔና ጓደኞቼ ወቅቶቹን በጉጉት እንከታተላቸው ነበር።የኔ ድምዳሜብዙውን ጊዜ በሀገራችን ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች በአንድ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ወይም ሲከራከሩ ላለመሸናነፍና ሁሌም በኔ መንገድ መሆን አለበት በሚል ግትር አስተሳሰብ በመያዝ ልዩነቶችን ተቀብሎ፣ በሚያስማሙ ሐሳቦች አብሮ ለመሥራት ባለመፈለግ በርካታ ስህተቶች ይፈጸማሉ። በ97 ምርጫ የተሳተፉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን አመለካከት በመከተል በወቅቱ ያገኙትን ድምጽ በመጠቀም (በፊት ከነበራችው 12 የፓርላማ መቀመጫ ወደ 170 አሳድገዋል፤ ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ አሸንፏል) በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መሥራት ነበረባቸው። በአንጻሩ እነርሱ ሁሉንም ካላሸነፍን በማለት አመጽ በማስነሳት ያለአግባብ የበርካታ ሰው ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኑ። ይህንን ሁኔታ ሳስታውስ፥ በደርግ ጊዜ የተካሄደውን በሁለት ግራ ዘመም ርዕዮተ አለም (አይዲዎሎጂ) በሚከተሉ ድርጅቶች (ኢሕአፓ እና መኢሶን) መካካል በተፈጠረውና በውይይት ሊፈታ ይችል በነበረው የሐሳብ ልዩነት ምክንያት የፈሰሰው ደም ብሎም ሊገነባ ይችል የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት መጨናገፉን አስባለኹ።እንደዚሁ ሁሉ የምርጫ 97 መጨናገፍም ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲ የመራመድን ተስፋ ያጨለመ ነበር። ምክንያቱም የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ የሆነው የሕዝቦች ፍላጎት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ አለመረጋገጡ የዴሞክራሲ ጅምሩ ማኮላሸቱን ያሳያል። 97 ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በተካሄደው 2002 ምርጫ 63 ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረው ከሁለት የፓርላማ ወንበሮች በስተቀር ሁሉንም ኢሕአዴግና አጋሮቹ አሸነፉ። ይህ ሁኔታ ለምን እንደተፈጠረ ቢጠና ጥሩ ትምህርት የሚሆነን ቢሆንም፥ ምናልባትም የምርጫ 97 አሉታዊ አስተዋጽኦ ይኖርበት ይሆን የሚል ሐሳብም ያጭርብኛል።ተስፋ አደርጋለኹ፥ ወደፊት በሀገራችን ማንኛውንም ልዩነቶች በውይይትና ሰጥቶ በመቀበል እሳቤ የማካሄድ ባህል ጎልብቶ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓትም ተመስርቶ ሕዝቦች በመረጡት መንገድ እንደሚተዳደሩ። ደግሞም ምክር ቤቶቻችን የሕዝብን ጥያቄ አንስተው የሚከራከሩበት እንጂ የጎማ ማህተም (rubber stamp) የማይሆኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠር፥ ተስፋ አደርጋለኹ።