By Godana
ቅዳሜ ሚያዚያ 6 ቀን 2015 ዓ/ም- ጀላል የሱፍ - ካርቱም ሱዳን - ከሰማያዊው አባይ ዳር።ሱዳን አሉኝ ከምትላቸው ወጣት የ’ቪዥዋል’ አርቲስቶች አንዱ ነው፥ ጀላል። ከሱዳን ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኘው እና በ 10 ሜትር ቁመት እና በ 5 ሜትር አርብ የተንጣለለው የስዕል ማሳያ አዳራሹ ለዓመታት በለፋባቸው የስእል ሥራዎቹ የተንቆጠቆጠ ነበር።ሚያዚያ 6 ቀን 2015 ዓ/ም ጀላል የሱዳን ቤተ-መንግስት አቅራቢያ በሚገኘው በዚሁ የስራ ቦታው ሳለ ነበር ወታደሮች በአካባቢው ሲሰባሰቡ የተመለከተው። ነገሩ ያለመደው ዓይነት እንቅስቃሴ ነበርና ስቱዲዮውን ዘግቶ በካርቱም ጫፍ ወደሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤት አቀና። በማግስቱ ሱዳን “ፈነዳች”። ከታች በምስሉ ላይ የምትታየውን ስቱዲዮውን ዘግቷት ሲወጣ፤ ግፋ ቢል በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚመለስ አስቦ ነበር። ጀላል ስለ ሱዳን ብሎም ስለካርቱም አውርቶ አይጠግብም - ምንም እንኳን እንደዋዛ ከተያዩ፤ ሱዳንመ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች በዚህ በያዝነው የሚያዚያ ወር ሁለት አመታት ቢቆጠሩም። ሱዳንን እና የእርሱን ትውልድ ሲያስብ እውቁን ማሃሙድ አብዱል አዚዝን ያነሳል። ከማሃሙድ ስራዎችም “መቼሊ ሁም” የተሰኘውን እና በግርድፉ ሲተረጎም “አትጨነቂ” የተሰኘው ሙዚቃው “የእኔ ትውልድ እየሰማ ነው ያደገው'፤ ግጥሙን በልቡ የማያውቀው የለም። ዘፈኑ የፍቅር ቢሆንም፤ አሁን ሱዳን ያለችበትን ሁኔታ ይገልፃል ብዬ አስባለሁ” የሚለው ጀላል ለዚህም ነው የወጋችን ዋና መተሪኪያ እንዲሆን የመረጠው። እኛም ከጀርባ ልናጫውተው ወደድን፤ የግጥሙን ጥቂት ስንኞችም በጀላል እርዳታ እንዲህ ወደ አማርኛ መለስናቸው። “ለዛሬ አትጨነቂ ውዴነገ ሳቅ ይሆናልናታገሺጭንቀትሽን በእንባሽ አትሸከሚውየሃዘን ወንዝ ማብቂያ የለውምና” በናይሮቢ ኬንያ በምትገኘው ጠባብ ስቱዲዮው ውስጥ ስለ “ሰማያዊው ሰው” በተነጋገርንበት እለት፥ ከተፋላሚ ኃይሎች አንዱ በሆኑት ጀነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር ለኹለት ዓመት በከበባ የቆየችውን ኤል ኦቢየድ ከተማን ማስለቀቁን አስታክከን በቅርቡ ወደ ካርቱም ለመመለስ ያቅድ እንደሆነ ጠየቅነው። “ትንሽ ይረጋጋ እንጂ እመለሳለሁ”።በየካቲት ወር የሱዳን ብሔራዊ ጦር ተፋላሚውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እየገፋ እና በርካታ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ መምጣቱን ተከትሎ ጀላል ወደ ካርቱም የመመለሱን ጉዳይ አውርዶ አውጥቶ የጨረሰ ይመስላል። “እመለሳለኹ፥ ጋለሪዬ ያለበት ሕንፃ በከባድ መሣሪያ ተመቷል፤ ወለሉ ላይም እሳት ተነስቶ እንደነበር ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቆ ከነበረ ቪዲዮ ላይ አይቻለሁ። ስእሎቼን አቃጥሎ ይሆን ወይስ ይትረፉ አላውቅም። ግን ተመልሼ ከዜሮ ጀምሬ እገነባዋለኹ”።ጀላል አሁን ያለበት “የመንፈስ ጥንካሬ” ላይ ከመድረሱ በፊት ሁለት ድንበሮችን አቆራርጧል።‘መንታዬ’ የሚለውን የአክስቱን ልጅ በጦርነቱ አጥቷል፥ ሙስሊም ማህጆብ’ን። ከሙስሊም ጋር ለመጨረሻ ግዜ የተያዩት ጀላል ን ወደ መተማ ድንበር አድርሶት የተመለሰ እለት ነው - ሰኔ ወር 2015 ዓ/ም። ጀላል ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ ለኹለት ወራት ካርቱም ቆይቷል። ውጊያው ሲያይል እና መሠረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ሲከብድ፥ አዛውንት ቤተሰቦቹን ሠርቶ ለማገዝ በፊት ወደሚያውቃት ኬኒያ ለመሄድ በማሰብ ለመሰደድ ወሰነ።“ሙስሊምን አብረን እንሰደድ ብዬው ነበር። እምቢ አለ። ህክምና ላይ ስለነበረ አቅም የለኝም ብሎ አሻፈረኝ አለ” ይላል ጀላል።ከአገሩ ሲወጣ ከአንድ የጀርባ ቦርሳ እና በቅርቡ እመለሳለሁ ከሚለው ተስፋ ውጭ የሰነቀው ነገር አልነበረም። በጦርነቱ የመጀመሪያ ወራት ከነበሩ ዘገባዎች አንዱ፥ ጦርነቱን ሸሽተው የተሰደዱ ሱዳናዊያን መኪኖቻቸው በታጣቂዎች ሲነዱ፥ ቤታቸውንም መኖሪያ አድርገዉት በማኅበራዊ ሚዲያ ታጣቂዎቹ ራሳቸው የሚያሰራጩት ይዘቶች ነበሩ። ይህንን ሱዳናዊያን ብቻ ሳይሆኑ መላው አለም አብሮ ተመልክቷል። በካርቱም ውስጥ የነበረውን ዘረፋ በተለይም በሌፍተናንት ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላት ይህንን ተግባር ይፈጽሙ ነበር።ጀላል ኢትዮጵያን ከጦርነቱ በፊት ጠንቅቆ ያውቃታል። ለስደት ጎዞው በተመለሰባት ወቅት ‘ተቀያይራ’ እንደጠበቀችው ይናገራል። “ኑሮ ተወዷል። በፊት ብዙ ወንጀል አልነበረም፥ መሪያቸውንም ‘ሚስተር ላቭ’ ይሉት ነበር” ይላል ጀላል። “መሪው ስለፍቅር ብቻ የሚያወራበት ግዜ ነበር”። ጀላል ከስደት በፊት ለመጨረሻ ግዜ ኢትዮጵያ የመጣበትን ወቅት መዘርዘር ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆን አልፈነዋል።አዲስ አበባ ከመድረሱ በፊት መተማ ላይ ወባ ቢጤ የያዘችው ጀላል ፥ በጎንደር አድርጎ አዲስ አበባ ሲገባ በጠና ታሞ ነበር። “ጎንደር ላይ ሁለት ቀን አድሬአለሁ፥ ምክኒያቱም አውሮፕላን ለመሳፈር የሚሆን አቅም እንኳን አልነበረኝም” ይላል።ለመሰደድ ሲወስን ለጀርመናዊ ወዳጁ ያጫወተው ጀላል - አዲስ አበባ ላይ የሚቀበለው ሰው እንዳለ እና ሃሳብ እንዳይገባው ነገረው። አዲስ አበባ ሱዳናዊ ሙዚቀኛ ወዳጁ ቢኖርም ከመሰደዱ በፊት ይቀበልሃል የተባለው ግን ኢትዮጵያዊው የወዳጁ ወዳጅ ነበር። አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ለስድስት ቀን ተኝቶ እየታከመ ሳለ ነበር ጀላል ከካርቱም አንድ የስልክ ጥሪ የደረሰው።“አካሌ በጠና ታሞ ነበር። ከዛ በላይ ግን ወንድሜ በጥይት ተመትቶ መሞቱን መስማቴ ዙሪያዬን አጨለመው” ይላል።ለስድስት ቀናት ተኝቶ ከሚታከምበት ሆስፒታል ከወጣ በኋላ ፒያሳ ወደሚገኘው የአዲሱ ወዳጁ ቤት አረፈ። ከሕመሙ ባልተናነሰ ከሞቃቷ ካርቱም ለመጣው ጀላል የአዲስ አበባ ብርድ ፈተና ነበር። ካረፈበት ቤት ጓሮ ሄዶ ፀሐይ ላይ መቀመጥ የእየ’እለት ልምምዱ ሆነ። በራሱ አንደበት ሲገልፅ “ጨለማ የሆነ ድባቴ ውስጥ ገባኹ። ልቤ ከበደ። የሙስሊም መሞት በጣም ጎዳኝ። ተስፋ ቆረጥኹ።”የእየ’ቀን ልምዱ ጓሮ ወጥቶ ፀሐይ መሞቅ ብቻ ሳይሆን አስተናጋጁ ወዳጁ ግራ ትከሻውን ቸብ ቸብ አድርጎ የሚለው ቃል መስማት ጭምርም ነበር። “ሰላምታ ይሁን ምን እንደሆነ ባላውቅም ‘አይዞህ’ ብሎ ትከሻዬን ይጎስመኝ ነበር” ይላል። ወዳጁ ጀላልን ወደ ስዕል ስራው እንዲመለስ እና ያንን ማድረግ ሐዘኑንም እንዲሽር እንደሚረዳው ለማስረዳት ቢሞክርም አልተሳካለትም፥ ጀላል አሻፈረኝ አለ።“አንድ ቀን በቀለም ተሞላ ሳጥን አምጥቶ ‘ለማንኛውም ይቀመጥ’ ብሎ ሄደ” ይላል። “በእየለቱ ፀሐይ ስሞቅ ከጀርባ ያለውን ግንብ እመለከታለኹ። ግንቡ ላይ የሚቀመጡትን እርግቦችንም አተኩሬ አያቸው ነበር”።ታዲያ በለመደው ቋንቋ ህመሙን ለመለጽ ሲነሳ ከወረቀት ወይም ከሸራ ይልቅ መተከዣ ጓሮውን ለሙራል ፥ በግንብ/ግድግዳ ላይ የሚሳሉ የስዕል ሥራዎች፥ ዘመቻ አጨው። ጀላል ካርቱም ውስጥ ከሚታወቅባቸው ሥራዎቹ አንዱ የሙራል ሥራዎቹ ናቸው። በተለይም በአብዮቱ ወቅት በካርቱም ጎዳናዎች ላይ በርካታ ሙራሎችን ስሏል።በታህሳስ 2011ዓ/ም በመላው ሱዳን ፈንድቶ በሚያዚያ 2011 ዓ/ም ሱዳንን ለ 30 ዓመታት ያስተዳደሩት ኦማር ሀሰን አል በሽር ከሥልጣን እንዲወገዱ ምክንያት የሆነው እና ሱዳናዊያን “ያልተጠናቀቀ” የሚሉትን አብዮት ያለ ጥበብ - በተለይም የካርቱምን ጎዳናዎች ካቀለሙት ሙራሎች ውጭ ማሰብ ከባድ ነው።በርካቶቹ የካርቱም ሰአሊያን- ጀላልን ጨምሮ - የልምድ ጥበበኞች አይደሉም። አምባገነናዊው የበሽር አገዛዝ ጫና ያልበገራቸው የሱዳን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት - በተለይም የካርቱም ዩኒቨርሲቲ - የነጻ ሃሳብ ማንሸራሸሪያ ደሴቶች ብሎም የነጠሩ ምሁራን መፍለቂያ ነበሩ። በርካታ የካርቱም ሰአሊዎችም የጥበብ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው የተጠበቡ ናቸው። ከሱዳን በዘለለ ስለ አፍሪካ ጥልቅ እውቀት አላቸው። በሱዳን “የፋይን አርት” ትምህርት ቤት የተማረው ጀላልም ሥራዎቹ ከካርቱም ውጭ እንደ ኪጋሊ፥ አዲስ አበባ፥ ሃምቡርግ ባሉ ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ተንጣለው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።ከካርቱም ውጪ ከሰራቸው ሌሎች ሙራሎቹ የሚለየውን እና የራሱ ነፀብራቅ የሆነውን “ልቡ የከበደውን” ሰማያዊውን ሰው በፒያሳ ጓሮ ላይ የፈጠረው ጀላል እንዲህ ሲል ይተርከዋል። “ልቡ ላይ ያለው ቀይ ምልክት የሙስሊምን ሃዘን የሚያመላክት ነበር። “ግድግዳ ላይ የማያቸው ርግቦችም የታሪኩ አካል ስለሆኑ፥ አንዱም ከላይ ያለው ነጭ ጨረቃም መጪውን የተስፋ ብርሃን እንዲወክል አድርጌ ፈጠርኩት”። በምስሉ ላይ ጥሎት በወጣው ስቱዲዮው ውስጥ ካሉት ወንበሮች አንዱን ከካርቱም የቀረችውን ብቸኛ ቁሳዊ ቅርሱን - የጀርባ ቦርሳውን - አኖረ። “ለምን ሰውየው ሰማያዊ እንዲሆን መረጥኽ?” ለሚለው ጥያቄም “ጥቁር ቀለም አልነበረኝም። ሰማያዊ እና [ሌሎች] ቀለሞችን ቀያይጬ ነበር ጥቁር ለመፍጠር የሞከርኹት። ግን ጥቁር ሰማያዊ ሆነ። በርግጥ ሰማያዊ ቀለም በአብዮቱም ሆነ በሱዳን ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቀለም ነው። እናም ሳልቀይረው ቀረኹ” ይላል።ጀላል ከሸሸው የሃገሩ ጦርነት ወዲያ፤ ዜጎቿ በራሳቸው ጦርነት የሚማቅቁባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ሰማያዊውን ሰው ፈትቶ ለቀቀው። በቀጣይ የጥበብ እርምጃዎቹ፥ ከራሱ አልፎ የመላው ሰላም እና ነፃነት ናፋቂ ሱዳናዊያንን የጋራ ሐዘን ብሎም ተስፋን መተረኪያው የሆነውን [“አኒክ ዶቱ”] ባለ ከባድ ልቡ ሰማያዊው ሰው ሆነ፥ በጥበብ ሥራዎቹ ውስጥ ሁሉ በሚባል ደረጃ ሰማያዊው ሰው አሻራውን ዛሬም ድረስ ያኖራል። ከ 12 ቀን የአዲስ አበባ ቆይታ በኋላ ወደ ዋነኛዋ መዳረሻው ናይሮቢ የዘለቀው ጀላል አዲስ ስቱዲዮ አደራጅቷል። አዲስ የተደራጀችው ስቱዲዮው መላው ግድግዳዋ በግሩም ስዕሎች ተሞልተዋል - አየሩ ደግሞ አሁንም ድረስ ከሱዳን እክስቶቹ በሚልኩለት እጣን ጭስ። በከተማው ውስጥ ኤግዚቢሽኖችን ያደርጋል። ናይሮቢ ከሱዳን የተሰደዱ በርካታ ጥበበኞች መሸሸጊያ በመሆኗ ጀላልም “ኮሚኒቲ” አግኝቷል።በሰማያዊው ሰው ጫና ስር የወደቁት የጀላል ሥራዎች አሁን በመላው ዓለም ይሸጣሉ።የአዲስ አበባው፥ የመጀመሪያው፥ ታሪካዊው ሙራል ግን - “ለልማት ተፈልጎ ፈርሷል”።
By Godana
በቅድሚያ የከበረ ሰላምታችን ይድረስ፥ እንኳን ወደ ጎዳና በሰላም መጡ!ጎዳናችን በበጎ ፈቃደኞች ተቋቁሞ የሚመራ፣ መሠረቱን ድረገጽ ላይ ያደረገ የብዙኅን መገናኛ መድረክ ነው።ጎዳናን ለመጠሪያነት ስንመርጥ የተነሳንበትን ዓላማ በአግባቡ እንደሚወክል በማሰብ ነው። ጎዳና ሰፊ መንገድ ነው፤ አንዱን ከአንዱ ሳይለይ መንገደኛውን ሁሉ የሚያስተናግድ፤ እንደቀጫጭን መንገዶች ለአቋራጭ ሳይሆን ለረጅም ጉዞ የሚመረጥ።ከዚህ አኳያ ነው ጎዳናችን አይነኬ የሚባል ርዕስ ሳይኖር ሀገራችንን ብሎም ትውልዳችንን ይረባሉ በተባሉ ሐሳቦች ላይ አካታች በሆነ፤ ለሥነ-ምግባር በመገዛት፤ በተለይም የተለያዩ ትውልዶችን የሚያሰናስል የውይይት መንገድ ለመፍጠር አልሞ የተነሳው።በአሁኑ ወቅትም እንደ ሀገር ብሎም እንደ ሕዝብ የተጋረጡብንን የፍትሕ፥ የሰብአዊነት እና የእኩልነት እጦት የወለዳቸውን ቀውሶች ለመጋፈጥ ብሎም በግለሰቦች እና በቡድኖች መካከል ያሉ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን በበሰለ ውይይት እንዲንጸባረቁ መደላድል መፈጠሩ አንገብጋቢ መሆኑን ጎዳናችን አምኖ በቁርጠኝነት የበኩሉን ለማበርከት መጥቷል።ላሰብነው የነጻ ሐሳብ መድረክ ባለሐሳቦች ሐሳባቸውን በመግለጻቸው ምክንያት ብቻ የሚያጋጥማቸውን ስጋት በመረዳት፥ በቅድሚያ ለባለሐሳቦች አንጻራዊ ሰላም ያለበትን አውድ ፈጥረናል።በተጨማሪም ጎዳናችን አጋርነት (solidarity) ቁልፍ እሴቱ ነው። በመሆኑም ሰብአዊነት፥ ፍትሕ እና እኩልነትን የሚረዳ፣ የሚያከብር፣ የሚደግፍ ብሎም የሚያጠናክር ባህልን ለማስፈን እንተጋለን።በተለይም አዲሱ ትውልድ ከዛሬው እውነታ በዘለለ ከቀደምት ትውልዶች የሚማርበት፥ ምክንያታዊነትን የሚያጸናበት እንዲሁም በራሱ መንገድ የግል ብሎም የማኅበረሰቡን ሕይወት የሚያሻሽልበትን አማራጭ ማፈላለጊያ ለመሆን ጎዳና ቁርጠኝነት አለው።ይህንን በማስመልከትም በቀጣይ ሳምንት ይፋ የሚደረገው የመጀመሪያው ልዩ የውይይት አጀንዳችን - በዚሁ በያዝነው ወር 20 ዓመት የሞላውን ምርጫ 1997ን እና በታሪክ ጥሎ ያለፈውን ውጤት መመርመርን መርጧል።ይህ ልዩ የውይይት አጀንዳ ወሩን ሙሉ የተለያዩ አንጋፋ እንዲሁም በምርጫው በቀጥታ የተሳተፉ የፖለቲካ መሪዎች፥ ሂደቱን የተከታተሉ ግለሰቦች ብሎም በተመረጡ ጉዳዮች ላይ የሙያ ዕይታቸውን የሚያካፍሉ ግለሰቦች የሚሳተፉበት ይሆናል።የዚህ ልዩ እትም ዋና ዓላማ ታሪክን ከመንገር በዘለለ ጉዳዩን መለስ ብሎ በጥልቀት መመልከት በመሆኑ፣ ተሳታፊዎች እስከዛሬ በጉዳዩ ላይ ከሰጡት አስተያየቶች በዘለለ በጥልቀት ሂደቱን ገምግመዋል፤ ቀጣይ ትውልድ ቢማርባቸው ብሎም ቢያሻሽላቸው ባሏቸው ስህተቶች ላይም ምክራቸውን ተይበዋል።በዚህም መሠረት ጽሑፎቹ ከምርጫው በፊት የነበረውን ኹኔታ በጥልቀት የሚያስቃኙ እንጂ የ'ነበር' ታሪክ ጠቃሽ ብቻ አይደሉም።ጎዳናችን የእናንተን ሐሳብ የሚቀበልበትን መንገድም አዘጋጅቷል። ወደ ድረ ገጻችን በመሄድ በዚሁ ባነሳነው ጉዳይ ላይ ያላችሁን አስተያየት፣ ትውስታ ብሎም ሂደቱ ይዞት የመጣውን በጎ ወይም አሉታዊ ውጤት የዳሰሱ አጫጫር ጽሑፎችን ሊልኩልን ይችላሉ። እኛም ይዘቱን ፈትሸን በድረ ገጻችን ላይ እናትመዋለን።ጎዳና በቀጣይ በተለያዩ አምዶች ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችንና ጉዳዮችን፣ ታሪኮችንና ነባራዊ ኹኔታቸውን የሚዳስሱ ሥራዎችን ከሕዝቡ ወስዶ ለሕዝቡ ያደርሳል። መወያያ፣ መነጋገሪያ፣ አንዱ በሌላው ጫማ ሆኖ የሚያይበትን አንጻር በመስጠት ይቀጥላል።እስከዛው የማኅበራዊ ገጾቻችንን በመከተል ይቆዩን! ጎዳናግንቦት 6፣ 2017 ዓመተ ምሕረት
By Godana
አልበሙን ያሳተመው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ነው። ከ 20 ዓመት በፊት አዲስ አልበም በዋነኝነት የሚደመጠው በካሴት ነበር፥ የተወሰነ ደግሞ በሲዲ። ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‘ያስተሰርያል’ የተሰኘ ሁለተኛውን አልበም ሲያወጣ ኢትዮጵያዊያን ታሪካዊ በተባለ ምርጫ ለመሳተፍ የሳምንት ግዜ ብቻ ነበር የቀራቸው።የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በወቅቱ የአንድ የራዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢ ነበሩ። ፀሃፊያችን ከ'ያስተሰርያል' እና ከምርጫው በተጨማሪ የወቅቱ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ አዲስ ክስተት የነበረው የኤፍኤም ራዲዮ ቴክኖሎጂ መምጣትን ተከትሎ የታዩ ልዩ ክስተቶችን አስታክከው ትዝታ እና ትዝብታቸውን ያስቃኙናል። ጸሀፊያችን የሚጠቀሙት የብዕር ስም "ፍ.ገ - ከአዲስ አበባ" በጊዜው በራዲዮ ዘፈን የሚመርጡ ወይም በአወዛጋቢ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች የሚጠቀሙትን የስም አመራረጥ ዘዴ የተከተለ ይመስላል። “አንባቢዎችዎ የትኛውን ሙዚቃ እያደመጡ ያንብቡዎት” ብለን? ጠይቀናቸው ነበር፤ ምላሻቸው 'ያስተሰርያል' የሚል ሆነ። ፍ.ገ ስለ ዘፈን ምርጫቸው እንዲህ ይላሉ፥“ያስተሰርያል የምርጫው ሳውንድ-ትራክ ነበር። በኮንሰርቶች ላይ ቴዲ እንዲዘፍነው በየሙዚቃው መሃል ይጠየቅ ነበር። ይዘቱም ብዙ ክርክር ያስነሳ ነው። በግልፅ አንድን ብሔር ያጥላላበት ነው ብለው የተቆጡ ብዙ ናቸው። የእርቅ ጥሪ ያቀረበበት እንጂ የሚያስቆጣ ነገር የለውም ብለው የተሟገቱለትም አልጠፉም።”ሙዚቃውን ለማድመጥ በቀኝ በኩል ያለችውን ቢጫ ምልክት ተጭነው ጽሑፉን ያንብቡ። በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ካልዎትም ያካፍሉን ዘንድ እንጋብዛለን። ጎዳና ጊዜው በ1996 መጨረሻ ወይም 1997 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ይመስለኛል፤ ዕለታዊ ፕሮግራማችንን ለማቅረብ ወደምንሠራበት የኤፍ.ኤም 97.1 የሬዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ስንደርስ ቴክኒሻኖቹ አጠገብ ባለው በር ላይ የተለጠፈ አዲስ ማስታወቂያ ትኩረታችንን ሳበው። እንዳይተላለፍ የተከለከለ ሙዚቃን ጠቅሶ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። ዘፈኑ የላፎንቴኖች "ባዴ ባዴሳ" ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ድምፃዊያኑ ዘፈኑን ቀድሞ በተጫወተው ዓለማየሁ እሸቴ ተከሰው በመረታታቸውና ፍርድ ቤት ዘፈኑ በሚዲያ እንዳይጫወት በማገዱ ነበር። ምንአልባትም በይፋ በፍርድ ቤት የታገደ የመጀመሪያው ዘፈን ሳይሆን አይቀርም። የዘፈን እገዳ ነገር ግን በዚህ አልቆመም። በተለይ 1997 የክልከላ ዓመት ነበር።በፍርድ ቤት ባይሆንም በጣቢያው ኃላፊዎች ውሳኔ ዘፈኖች እንዳይተላለፉ መደረጋቸው አዲስ ነገር አልነበረም። የኤፍ.ኤም 97.1 መከፈትን ተከትሎ ብዙ ወጣቶች አዳዲስ ሙዚቃዎችን በገፍ የመሥራት ልማድ አምጥተው በየዕለቱ ሲዲዎች ወደ ጣቢያው ይጎርፉ ነበር። ነገር ግን የተደመጡት ጥቂቶቹ ነበሩ። አንዳንዶች ዝና ፍለጋ ወቅታዊ ኹነቶችን ተንተርሰው የይድረስ ይድረስ ይሠሩ ስለነበር፣ ሙዚቃዎቹ አሸማቃቂነታቸው ያመዝናል።እናም ብዙዎቹ እንዳይተላለፉ በቃል ትዕዛዝ ታገዱ። በተለይ ፋሽን ሆኖ የነበረው ለታዋቂ ሰዎች መዝፈን አመራሮቹን ክፉኛ አስመረረ። ለነገሩ አድማጮችም ተሰላችተው ነበር። መጨረሻ ላይ ዘፈኖቹ እንዲቆለፍባቸው ትዕዛዝ የተሰጠው ለቻቺ ታደሰ እና ለጋሽ አበራ ሞላ የተዘፈኑ ሁለት የተለያዩ ዘፈኖች ስቱዲዮ የመጡ ሰሞን ነው። እንደውም የጣቢያው ኃላፊ ከነበሩት መካከል አንዱ አንጋፋው ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር "በዚህ ከቀጠለ ነገ ደግሞ ጎርፌ ጎርፌ ብለው ሊዘፍኑ ይችላሉ" ብሎ ምሬቱን በቀልድ እንደነገራቸው የቢሮ ባልደረባዎቹ ነግረውኛል።የቃል ዕገዳው በዚያ አልቆመም። የዚያን ሰሞን የሞኒካ ሲሳይ "ሸክሽክ ዝም ብለኽ" የተሰኘው ሙዚቃ ባህል የሚፃረር ነው ተብሎ መከልከሉ ስቱዲዮ አካባቢ ተወራ። ጥቂት ቆይቶ ጎሳዬ ተስፋዬ ተረኛ ሆነ። "ላሊበላ" በተሰኘው አዲስ ነጠላ ዜማው ያሞገሳቸው አሚናዎች ‘በማይገባን ስም ጠርቶናል’ ብለው ቅሬታ በማቅረባቸው ዘፈኑ አይሂድ ተባለ።አየር ላይ የማይውሉት እነዚህ እንዳይተላለፉ የተባሉት ዘፈኖች ብቻ አይደሉም። አንዳንዴ የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዎቹ ወይም ጋዜጠኞቹ ከአመራር ወይም ከአድማጭ ሊመጣባቸው የሚችለውን ጫና ፍራቻ ወይም አላስፈላጊነቱን አምነውበት የማይለቁት ሙዚቃ ይኖራል። ለምሳሌ የሰለሞን ተካልኝን ‘ዜሮ ዜሮ’ ላለማጫወት ሁለቴ ማሰብ አይጠበቅም። የማርታ አሻጋሪ "መንገደኛው ልቤ" ከተላለፈ ከበላይ ውሳኔ በፊት ስቱዲዮው በአድማጭ የቅሬታ ስልክ እንደሚጨናነቅ ግልፅ ነው።የሆነው ሆኖ “ይሄ ይቅረብ፣ ይሄ ክልክል ነው” እያልን በቃል እየተግባባን መሥራቱን እንደቀጠልን የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቀዳሚው ማስታወቂያ ሆኖ ተለጠፈ። ቀጣዩን ትዕዛዝ ያስለጠፈው ደግሞ የምርጫ 97 ሞቅታ ሆነ።በምርጫው ሰሞን የሚዲያዎች ውጥረት ከፍ ያለ ነበር። የምርጫ ተፎካካሪዎች ሐሳባቸውን እንዲገልፁ የተሰጣቸው የአየር ጊዜ ቀድሞ ቢጠናቀቅም በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለተመራጮቹ በሬዲዮ መወራቱ አልቀረም። በመዝናኛ ፕሮግራሞች ወይም በዘፈን ምርጫ ዝግጅቶች ከአድማጮች ጋር ይደረጉ የነበሩ የአየር ላይ ገራገር ጨዋታዎች ርዕሶች ወደ ምርጫው ያመሩ ነበር። ይህ ደግሞ የአቅራቢዎቹን ፈተና አብዝቷል። አድማጮች በቀልድ መልክ ምርጫውን አያይዘው ለሚያነሱት ሐሳብ አቅራቢው ምን መልስ መስጠት እንዳለበት ግራ ሲገባው ይሰማል። የቴክኒክ ችግር እንደገጠመ አስመስሎ ስልኩን ማቋረጥ የተሻለው አማራጭ እንደነበር በብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል።ወደ ዘፈኑ ጉዳይ እንመለስ። የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም በወጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ በሬዲዮ ጣቢያው ስቱዲዮ ሌላ ማስታወቂያ ተለጠፈ። "ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ዘፈኖች እንዳይጫወቱ ተከልክለዋል" ተባለ። ዘፈኖቹ ሦስት፣ ባለ ዘፈኑ አንድ ሰው ነው። ዝርዝሮቹ ያስተሰርያል፣ ሼመንደፈር እና ካብ ዳህላክ፤ ዘፋኙ ደግሞ ቴዲ አፍሮ።ትዝ እንደሚለኝ ቀድመን የተወያየነው በዘፈኖቹ ላይ ነው። "ያስተሰርያል ይሁን፣ ሌሎቹ ምን አደረጉ?" የሚል ጥያቄ ተነሳ። "ካብ ዳህላክማ እንዴት በመንግሥት ሚዲያ እንዲተላለፍ ትጠብቃላችሁ፣ ባይሆን የሼመንደፈር ግራ ያጋባል" ብለው አስተያየት የሰጡም ነበሩ። የሆነው ሆኖ እገዳው ጥብቅ ስለነበር እነ ያስተሰርያል እንደ ከዚህ በፊቶቹ እስረኛ ዘፈኖች በቸልተኛ ወይም በጀብደኛ አቅራቢ ለሰከንዶች እንኳ አየር ላይ አልዋሉም። በውዝግብ ታጅቦ የተከናወነው ምርጫ 97 በአስከፊ ሁኔታ ሲደመደም ሚዲያው ላይ ጥሎት የሄደው የፍርሃት ደመና በቀላሉ የሚገፈፍ አልነበረም። ለእኛ ለመዝናኛ ጉዳዮች አቅራቢዎቹ እንኳ ወደ ቀድሞው ስሜት መመለስ ከባድ ሆኖብን ነበር።ከዚያ በኋላ በነበሩ ሁለት ዓመታት በይፋ የተከለከሉ ሙዚቃዎችን አላስታውስም። ነገር ግን ያ በቀላሉ ያልተገፈፈው ፍርሃት ጋዜጠኞቹን ከልክ ላለፈ ጭንቀት ዳርጓቸው ነበር። እንደሚታወሰው ከምርጫው በኋላ በአሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ ዝነኛ ድምፃዊያን ወደ አደባባይ ወጥተው መንግሥትን ሰድበዋል። ተቃውሞ አዘል ሙዚቃ የሠሩም አልጠፉም።በአንዱ ቀን ስቱዲዮ ቁጭ ብለን አንዱ ቴክኒሻን አየር ላይ የሚሄደውን የአንድ ተወዳጅ አርቲስት ሙዚቃ እየሰማ ጥያቄ አነሳ። "እንዴ የእገሌ ሙዚቃ ይሄዳል እንዴ?" አለን- አሜሪካ የሚኖርን ድምፃዊ ጠቅሶ። ግራ ተጋብተን "ምን ችግር አለው?" አልነው። "አይ የሰሞኑ ተቃውሞውና የዘፈነው የስድብ ዘፈን ድንገት አሳግዶት እንዳይሆን ብዬ ነው" አለ። ምላሽ ባንሰጠውም በመጠኑም ቢሆን ፍርሃቱን ሳያጋባብን አልቀረም።በእርግጥ ስለዚያ ድምፃዊም ይሁን አሜሪካ ስላሉት "አርበኛ" አርቲስቶች እስከማውቀው ድረስ ከበላይ አካል የመጣ አንድም እገዳ አልነበረም። ነገር ግን አንዳንድ አቅራቢዎች የአንዳንድ ዘፋኞችን ሥራዎች ለማቅረብ ፈራ ተባ ሲሉ ታዝቤአለኹ። በተቃራኒው የእነዚያን "አርበኛ" አርቲስቶች የቆዩ ሙዚቃዎች ደጋግመው ያቀረቡ የመንግሥት ተቃዋሚ ጋዜጠኞችና ቴክኒሻኖችም አልጠፉም። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መቱ እንደ ማለት ነው። የአርቲስቱን የአርበኝነት ውለታ በጥቂቱ እየመለሱ በዚያውም መንግሥትን ያበሽቃሉ።ያኔ ባህር ማዶ ሆነው የተቃዋሚነቱን ጎራ በይፋ ሲያቀጣጥሉ ከነበሩ አርቲስቶች መካከል ሻምበል በላይነህ እና ፋሲል ደሞዝ ይጠቀሳሉ።በበኩሌ፥ ዘፈን ሁሉ አየር ላይ መውጣት አለበት ብዬ አላምንም። የጥበብ መመዘኛውን ቢያልፍ እንኳ የሚያስተላልፈው መልዕክት በሚገባ መታየት ይኖርበታል። በዚህ በኩል ከሌሎች ጋዜጠኞች የሐሳብ ልዩነት አልነበረንም። የምንለያየው በዘፈኑ የተላለፈውን ሐሳብ በምናይበት መነፅር ነው። የዘፈን ክልከላዎቹ አለመግባባት የሚፈጥሩትም በዚህ የተነሳ ነበር። "ካብ ዳህላክ"ን ምሳሌ እንውሰድ። ከአመራሮች ሰማኹ ያለ አንድ ጋዜጠኛ እንደነገረኝ፥ ዘፈኑ የታገደው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የተሰበረው በዝሆኖች ፀብ ነው በማለቱ ነው። ለብዙዎች ይህ የማያከራክር እውነታ ቢሆንም ለወቅቱ ፖለቲከኞች ግን የሚዋጥ አልነበረም። ኢትዮጵያ የተወረረ ድንበሯን ለማስመለስ ተገዳ ወደ ጦርነት እንደመግባቷ ለተሰበረው ድንበር ሁለቱም ዝሆኖች እኩል ሊወቀሱ አይገባም ባይ ነበሩ። የሆነው ሆኖ መንግሥት የሚያይበት መነፅር ዘወትር አሸናፊ ስለሚሆን፣ የጋዜጠኞች ክርክር ከጣቢያው በረንዳ የሚያልፍ ውጤት አልነበረውም።"ያስተሰርያል" በመንግሥት ተቃዋሚዎች የተለየ ቦታ ነበረው። ቴዲ የልባቸውን እንደነገረላቸው የሚያምኑ ነበሩ። እንደ "በ17 መርፌ" እና "ለውጥ መቼ መጣ" የሚሉ ውስን የዘፈኑን ሐረጋት እያጎሉ ለቅስቀሳ ባስ ሲልም ለጥላቻ የተጠቀሙበት ጥቂት አልነበሩም።ዘፈኑ በዋናነት ያስቆጣው የኢሕአዴግ ደጋፊዎችን በተለይ ደግሞ የትግራይ ተወላጆችን ነው። የቁጣቸው ማጠንጠኛ በአመዛኙ አሁንም ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ስንኞች ናቸው። በወቅቱ ለሳምንታት በዘፈኑ መከራከራችንን አስታውሳለኹ። እዚህ ላይ በሁለቱም ወገኖች የነበሩ ክርክሮችን አንኳር ነገሮች ከራሴ አቋም ጋር አያይዤ ልዘርዝር።እኔ፥ በሁለቱም ጎራ የተሄደበት ፅንፍ ተገቢ እንዳልነበር ይሰማኛል። ከዘፈኑ ጀርባ የነበሩ የተዳፈኑ ፍላጎቶችና ጥላቻዎች ምክንያት ሆኑ እንጂ ዘፈኑ ብቻውን የምርጫው ሳውንድ ትራክ የመሆን በቂ ምክንያት አልነበረውም ባይ ነበርኩ። በተመሳሳይ የትግራይ ሰዎችን በዚያ ልክ የሚያስቆጣ ነው ብዬም አላምንም።የ’ያስተሰርያል’ ሐሳብ እርቅና መዋደድ ነው። ቴዲ “የተተኩት መንግሥታት ሁሉ ይቅር ከመባባል ይልቅ መጠፋፋትና መወቃቀስን መርጠዋል” ባይ ነው። በ17 መርፌ ምሳሌነት በተገለፀው የ17 ዓመት ትግል፣ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግም ቢሆን በእርቅ፣ ምህረትና ይቅር መባባል ላይ ለውጥ እንዳላመጣ ይጠቅሳል። የመንግሥት ደጋፊዎች ይህን በተለየ መልኩ ይተረጉሙታል። የ"ለውጥ መቼ መጣ" ገለፃው መንግሥት በልማቱም ሆነ በሌሎች በሚመሰገንባቸው ዘርፎች ሁሉ የተገኘውን ስኬት ለመካድ ተፈልጎ ነው ይላሉ። በመርፌ ስፌት የተጠጋገነው ቁምጣ የተነሳውም በትግሉ ላይ ለማፌዝ እንደሆነ ያነሳሉ።በተቃዋሚዎች በኩልም ዘፈኑ የመንግሥት ደጋፊዎችን ማስቆጣቱን እንደ ምቹ አጋጣሚ ወስደው ቁንፅል ሐሳቦችን ሲያጎሉ ታዝቤያለኹ። ብዙ ጊዜ የጀመርናቸው ክርክሮች መቋጫ አልነበራቸውም። ቴዲን የሚያወግዙት "ሌላ ዓላማ ያለው ነው" ሲሉ የተደሰቱበት ደግሞ "ነገረልን" ዓይነት ስሜት የሞላቸው ምክንያት አልባ መደምደሚያዎችን ይሰጡ ነበር።የቴዲ ዘፈኖች ምርጫ 97 ካለፈ ዓመታት በኋላም ቢሆን እገዳቸው አልተነሳም። ለመጀመሪያ ጊዜ የግል ኤፍ.ኤም ጣቢያ ፈቃድ መሰጠቱን ተከትሎ ዛሚ እና ሸገር ኤፍ.ኤም ስርጭት ሲጀምሩ "ሼመንደፈር" እና "ካብ ዳህላክ" የአየር ላይ ነጻነታቸውን አውጀዋል። "ያስተሰርያል" ግን እንደተቆለፈበት ጥቂት ቆይቷል። እስከማስታውሰው ድረስ ከሚሌኒየሙ በኋላ በነበሩ ቀዳሚ ዓመታት እጅግ አለፍ አለፍ ብሎ ዘፈኑ ይለቀቅ ነበር።ምርጫ 97ን ያጀበ አንድ ሙዚቃ ይነሳ ከተባለ ያለ ጥርጥር የሚጠቀሰው "ያስተሰርያል" ነው። ቴዲን ከለበሰው የኮከብ ድምፃዊነት ኮት ላይ "የነጻነት አርበኛነት" ካባ እንዲደርብ ያስቻለው ይሄው ሥራ ነው። በእርግጥ "አርበኝነቱ" ዋጋም አስከፍሎታል። ኮንሰርቶቹ በፈቃድ ምክንያት ተከልክለዋል። የተፈቀዱት ላይም አወዛጋቢውን ዘፈን በመድረክ እንዳያቀርብ ክልከላ ተጥሎበታል። አድናቂዎቹ በኮንሰርቶች መሃል ዘፈኑን በጩኸት እያዜሙ እንዲያቀርበው ቢገፋፉትም ቴዲ መዘዙን በመፍራት ይመስላል እያሳሳቀ ማለፍን መርጧል።የምርጫው ጣጣ አልፎ የታሰሩት የተቃዋሚ አመራሮች ከተፈቱና ሚሌኒየሙ ከተከበረ በኋላ ቴዲ በመኪና ሰው መግጨት ተከስሶ እስር ቤት እንደገባ አይዘነጋም። ያኔ በርካታ የድምፃዊው አድናቂዎች ክሱ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ያምኑ ነበር። "ያስተሰርያል" ያመጣበት መዘዝ ለእስር እንደዳረገውና መንግሥት በቀሉን እየተወጣበት መሆኑን ይገልፁ ነበር።ቴዲ ከያስተሰርያል በኋላ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ያነሳበት ሌላኛው ሙዚቃው "ናዕት" የተሰኘው ይመስለኛል። እንግዲህ ፖለቲካ አዘል ተቃውሞውን በሙዚቃ ለመግለፅ 18 ዓመታት አስፈልገውታል ማለት ነው።የዘፈን ክልከላ ጉዳይ ከምርጫ 97 ግለት መብረድ በኋላ አብሮ ተቀዛቅዟል። የኤፍ.ኤም 97.1 ስቱዲዮን እስከለቀቅንበት ጊዜ ድረስ ተጨማሪ የክልከላ ማስታወቂያ አልገጠመንም። ይሁን እንጂ የወጡ ሙዚቃዎች ሁሉ ይተላለፉ ነበር ማለት አይደለም። አመራሮቹም ትዕዛዝ ማውረድ አላስፈለጋቸውም። ጣጣ የሚያመጣውን ዘፈን አስቀድሞ ማወቅና መጠንቀቅ ለጋዜጠኞች የተተወ የስቱዲዮ ሥራ ሆኖ ቀርቷል።
By Godana
አቶ አንዷለም አራጌ በምርጫ 1997 ወቅት ወደፊት ጎልተው ከወጡ ወጣት ፖለቲከኞች መካከል ናቸው። በወቅቱም የቅንጅቱ ጥምረት አባል የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አባል ነበሩ።አንዷለም ካለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ወደ ዘጠኝ ዓመት የሚጠጋውን በእስር አሳልፈዋል። ቀጥሎም በ2009 ዓ.ም የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በከፍተኛ አመራርነት የመሩት አንዷለም፣ በ 2015 ዓ.ም ኢዜማን ለቀው ወጥተዋል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ የፒኤችዲ ጥናታቸውን ያካሂዳሉ፤ ራሳቸውንም “አሁን የሙሉ ግዜ ተማሪ ነኝ” ሲሉ ይገልፃሉ። አንዷለም በዚህ ሰፊ ጽሑፋቸው ከምርጫው ወቅት በዘለለ ያለፉትን 20 ዓመታት በዝርዝር የፈተሹ ሲሆን፣ ለነገም መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ በመውጫቸው ላይ አስፍረዋል። መጣጥፋቸውን "የጥላሁን ገሰሰን ቆሜ ልመርቅሽን እያደመጣችሁ አንብቡልኝ” ባሉት መሰረት በቀኝ በኩል ያለውን ቢጫ ምክልት በመጫን ምርጫቸውን ትቀበሉ ዘንድ ብሎም መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ እኛም ጋበዝን። ጎዳናገና ትንሽ ልጅ እያለሁ ነበር፣ ከትውልድ አካባቢዬ ርቄ አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ ከአያቴ ጋር መኖር የጀመርኩት። በካቴድራሉ መካነ-መቃብር ስፍራ እመለከታቸው የነበሩት የዐርበኞችና የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ሃውልቶች ላይ የተጻፉት አጫጭር፣ ግን ጠጣር መልእክት ያላቸው ጥቅሶች ባነበብኳቸው ቁጥር እንደ ዐዲስ መንፈሴን ያስደስቱት ነበር። አካባቢው ላይ ያረብበው ጸጥታ ስለ ጥቅሶቹም ኾነ በአጭሩ ስለተጻፈው ህይወት ታሪካቸው በአርምሞ የማሰላሰል ነፃነት ስለሚሰጠኝ እወደዋለሁ፡፡ በአንዳንዶቹ መልእከቶች ደግሞ፣ የልጅነት አእምሮዬ በሚያስበው ልክ እየተፈላሰፍኩ፣ ከአንዱ ሃውልት ወደ ሌላው ተዘዋውሮ መጎብኙቱ ያስደስተኝ ነበር፡፡ መቼም፣ የማይዘነጋኝና ገና በ12 ዓመቴ ወደ ፖለቲካው ዓለም እንድሳብ ያደፋፈረኝ በእውቁ የመኢሶን ሰው ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ የመቃብር ስፍራ ላይ ተጽፎ ያነበብኩት ጥቅስ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-“የተራበ፣ የተጠማና የተጨቆነ ሕዝብ የሚያጠፋው ጊዜ የለውም፣ ተነሱ!”የ5ኛ ክፍል ተማሪ ኾኜ ስለ ጀግናው አብዲሳ አጋ በዐማርኛ መማሪያችን መጽሐፍ (Text Book) ላይ ተጽፎ ያነበቡሁት ታሪክ ደግሞ፣ ‘የሀገር ፍቅርን አስተማረኝ’ ብል ግነት አይደለም።ሌላው፣ ያስተሳሰብ አድማሴን የገራው፣ በዚያ በመቃብር ቤት ከአያቴ ጋር ይኖር የነበረው አጎቴ ትቷቸው የሄዱትን የፖለቲካ መጻሕፍት ማግኘቴ ነው፡፡ አጎቴ፣ የኢሕአፓ አባል በመኾኑ ነው መሰለኝ፣ በርካታ በፕሮግረስ ማተሚያ ቤት የታተሙ ጥራዞችን ስብስቦ ነበር፡፡ እኔም እነዚያን መጽሐፍት በቻልኩትና በተረዳሁት መጠን ማንበቤ አልቀረም።በነገራችን ላይ፣ በቤተ-ክርስትያን ግቢ ውስጥ መኖር በራሱ፣ የህይወት ትርጉምን ማፈላለግ ያስተምራል። ጠዋት ክርስትና የሚነሱ ህጻናት፣ ከሰዓት የቀብር ሥርዐት፣ ምሽት በተክሊል ጋብቻ የሚጣመሩ ጥንዶች የሚመላለሱበት ስፍራ ነውና፡፡ ይህ ሁኔታም፣ ሞት እና ህይወት በአንድ ቀን ሲዘከሩ እየተመለከትኩ እንዳድግ አድርጎኛል።እነዚህ ኹነቶች ሊኾኑ ይችላሉ፣ ወደ ፖለቲካው በመግባት ለአንዳች ቁም ነገር መታገል እንዳለብኝም ኾነ የሚያስከፍለውን ክቡድ ዋጋ ገና በለጋ ዕድሜዬ ጀምሮ እንዳሰላስለው የተጫኑኝ።ምርጫ-97ን በትውስታበ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ሀገር ዐቀፍ ምርጫ 20 ዓመታት ወደኋላ ተመልሼ ምልከታዬን እንድዳስሰው በጎዳና መድረክ አዘጋጆች ስጠየቅ፣ ፈጥኖ ወደ አእምሮዬ የመጣው በዚሁ ወር 17ተኛ ዓመቱን ለሚያከብረው ልጄ ስለ ክስተቱ “አስረዳ?” ብባል፣ ‘ከየት ነው የምጀምረው?’ የሚለው ጥያቄ ነበር።እናም፣ ቢያንስ 60 ዓመታትን ወደኋላ ሄዶ ከየካቲቱ አብዮት መንደርደር ይጠይቃል ብዬ አስብኩ……ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት መጀመሩ እና በተለምዶ “የታኀሣስ ግርግር” ተብሎ የሚጠቀሰው የ1953ቱ መፈንቅለ-መንግሥት፣ በወቅቱ የነቁ ኢትዮጵያውያን ለለውጥ እንዲነሱ ዐይን ገላጭ እንደነበረ አይረሳም፡፡ ይህን ተከትሎም፣ በተማሪዎች እና በመምህራኖች መሃል የተፈጠረው ፖለቲካዊ መናበብ፣ የተማሪዎች ማኀበር እና በውጪ ሀገራት በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቅ ብቅ ማለት፣ በተለያዩ መጽሔቶች ንጉሣዊ ሥርዓቱን እየነቀፉና እያጋለጡ የሚሰናዱ መጣጥፎች ከመብዛታቸው ጋር ተደማምሮ የ1966ቱን አብዮት አዋልዷል ማለት ይቻላል፡፡ “መሬት ላራሹ”፣ “የብሔር ጭቆና” እና ሕዝባዊ መንግሥት” የሚሉ ጥያቄዎች ደግሞ ከፊት የሚቀመጡ ማታገያ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ በአጭሩ፣ በሀገራችን የተንሰራፋው ድህነትን እና የመደብ ጭቆና፣ በድኀረ-ጣሊያን ወረራ የዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ደጃፍ የረገጡ ዜጎች፣ ሥር-ነቀል የለውጥ ጥያቄ እንዲያቀነቅኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ኹነትም አብዮቱን አፋጥኗል፡፡ወደ አጀንዳችን ስንመለስ፣ ስለ ምርጫ-97 ለመረዳትም ኾነ፣ ዛሬም ድረስ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ለመገምገም የሚፈልግ ሰው፣ መነሻው ከመልከ-ብዙው የየካቲቱ አብዮት ቢኾን የተሻለ ይመስለኛል። ከሁለት ሺሕ ዓመት በላይ የቆየውን ንጉሣዊ ሥርዐት የገረሰሰው እና ቀጥሎ ለመጣው የወታደራዊ አገዛዝ በር የከፈተው ይኸው ክስተት ነውና።የወታደሩን ደሞዝ ጥያቄ ተንጠላጥሎ ወደ ሥልጣን የመጠው በኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም እና በጓዶቻቸው የሚመራው ደርግ፣ ለ17 ዓመታት ያደረሰው ጭቆናና ጅምላ ግድያም እጅግ አሰቃቂ በመኾኑ፣ በከተማ እና በገጠር ብርቱ ተቃውሞ አስከትሏል፤ ትጥቅ ትግልን ጨምሮ።በዘመነ-ደርግ በጠብ-መንጃ የሚፋለሙት የፖለቲካ ቡድኖች ወደ 17 የሚጠጉ ቢኾኑም፤ ዋንኛዎቹ በወቅቱ የኢትዮጵያ አንድ ክፍለ ሀገር የነበረችውን ኤርትራን ለማስገንጠል የሚታገለው “ሕዝባዊ ግንባር- ሻዐቢያ” እና “ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት)” ነበሩ።ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ ይሠሩ የነበሩት ሕወሓት እና ኢሕዴንም በ1981 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)” በሚል ስም አንድ ደርጅት መሰረቱ።በ1982 ዓ.ም ከኢሕዴን በወጡ የኦሮሞ ተወላጆች የተመሰረተው ኦሕዴድም የግንባሩ አባል ኾነ፡፡በ1983 ዓ.ም ወርሃ ግንቦት ኢሕአዴግ ጦርነቱን አሸንፎ መላ ሀገሪቱን ተቆጣጠር፡፡ ብዙዎቻችንም፣ ‘በኢትዮጵያ የአምባ-ገነን ሥርዐት አክትሞ፣ ዐዲስ የነፃነት ፀሀይ ሊወጣ ነው’ ብለን ተስፋ አደረገን።እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ የ1966ቱ አብዮተኞች (“የካቲታውያን”) ትውልድ ተጋሪው ኢሕአዴግ፣ ከደርግ (ከኢሕዴሪ) መንግሥት የከረረ ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ-ዓለም አቀንቃኝ የነበረ መኾኑ ነው። ወደ መጨረሻዎቹ ዓመታት፣ የምዕራቡ ዓለም፣ ከሶቪየት ሕብረት እና ተከታዮቿ ጋር የገባበትን “ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት (Cold War)” በማሸነፉ፣ ሰልፉን አስተካክሎ ከምዕራባውያኑ ጋር ጠንካራ ግንኙነትን ፈጠረ፡፡ ይህን ተከትሎም፣ ከለውጡ ጋር የሚሄድ ትርክት ለማንበር “ዴሞክራያዊ ሥርዐት”ን የሚሰብክ ድርጅት ኾኖ በቅ አለ። አልፎ ተርፎም፣ በሽግግሩ ቻርተርም ኾነ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የመደረጃትና ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብቶች መከበራቸውን የሚያትቱ ቀልብ-ሳቢ አናቅጽትን አሰፈረ፡፡በዚህም፣ እኔን ጨምሮ፣ በርካቶች በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የሰላማዊ ትግል ፖለቲካን ተቀላቀልን።ይሁንና፣ የተቃውሞ ጎራው ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ አያሌ መስዋትነትን ቢከፍልም፤ በውስጣዊና በውጫዊ ተግዳሮቶች እስከ ምርጫ-97 ዋዜማ ድረስ መንግሥት ለመቀየር የሚያስችል ቁመና መፍጠር አልቻለም ነበር።“ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ”ምርጫ-97 ከመድረሱ በፊት አያሌ ምሁራን እና ልኂቃን ከፍ ያለ ቁጥር የነበራቸውን ተቃዋሚ ድርጅቶች “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” በሚል ኃይለ-ቃል ወደ አንድ እንዲመጡ ግፊት ያደርጉ ነበር፡፡ እነዚህ በጎ ውትወታዎችም በ1996 መጨረሻ የ14 ፓርቲዎች ስብስብ የኾነውን ህብረቱን እና በ1997 ዓ.ም መጀመሪያ 4 ፓርቲዎችን ያቀፈውን ቅንጅትን አዋለዱ፡፡ምርጫው የተሻለ ስለ መኾኑበእኔ አረዳድ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከምርጫ-97 ፊት ከመቆሙ በፊት፣ መንገድ የጠረጉ አራት ገፊ-ምክንያቶች አሉ፡፡የመጀመሪያው፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የእንግሊዝ እና የአሜሪካ መንግሥት አዲስ አበባ ባሉ ኤምባሲዎቻቸው በኩል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ያለሰለሰ ጉትጎታ ማድረጋቸው ነው።ሁለተኛው፣ በአንድ በኩል፣ ‘ተቃዋሚዎች እርስ-በርስ የማይስማሙና አንድነትን መፍጠር የማይችሉ ደካማ ናቸው’ ተብሎ መታሰቡ፤ በሌላ በኩል፣ ኢሕአዴግ ‘ተፎካክሮ የሚረታኝ ኃይል የለም’ ብሎ ማመኑ ነው፡፡ሦስተኛው፣ የኢሕአዴግ አስኳል የኾነው ሕወሃት በ1993 ዓ.ም በውስጡ ታላቅ መሰንጠቅ ተፈጥሮበት በደርዘን የሚቆጠሩ ተጽእኖ ፈጣሪ አመራሮቹን ማሰናበቱ ነው፡፡ በወቅቱ፣ የሕወሃት እና የኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍስ ይማር!) ለአውሮፓ ህበረት እና ለአሜሪካ መንግሥት ‘ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳናካሄድ ሰንገው የያዙን አፈንጋጮቹ አመራሮች ናቸው’ የሚል ወቀሳ ይስነዘሩ ስለነበረ፣ እሳቸው እና ጓዶቻቸው ዴሞክራት መኾናቸውን ለማሳየት አብዘተው ይፈልጉ ነበር፡፡አራተኛው፣ ከ1984-1998 ዓ.ም ጥቅምት ወር ድረስ የነበሩት ነፃ ሚዲያዎች (ጋዜጦች እና መጽሔቶች) ከእነ ድክመታቸውም ቢኾን፣ ሕዝቡን በማንቃቱ እና ኢሕአዴግን በማጋለጡ ረገድ ሰፊ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ ግፊት መፈጠራቸውን ጨምሮ፤ ሕዝቡ ለለውጥ ያለው መሻት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ ምርጫ-97ን በታሪክ ከፍታ ላይ እንዲቀመጥ አደረገው።መስከረም ጠባቀደም ብሎ ከተመሰረተው ከህብረት በተጨማሪ፤ በ1997 ዓ.ም ጥቅምት ቅንጅት ተመሰረተ፡፡ ይህ ሁኔታም፣ ምርጫው በሀገሬውም ኾነ በውጭ መንግሥታት ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰብ አደረገ፡፡ከምርጫው ስድስት ወራት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ሚድያዎችና የስብሰባ አዳራሾች የፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭ ክርክር በቴሌቪዥንና ሬዲዮ በቀጥታ መሰራጨት መጀመሩ ትኩረቱን በእጅጉ አናረው። ይህን ተከትሎም፣ ገበሬው ሬድዮውን በጆሮው ደግኖ፣ ከተሜው ፊቱን እንደ አሸን በፈሉት ጋዜጦች ሸፍኖ፣ ኮረዳዎችና ጎረምሶች ወደ ፊልም ቤት ከመሮጥ ይልቅ፣ የሀገራቸውን ሁኔታ ለመረዳት የሚራወጡበትን ተስፋ ሰናቂ ድባብ ፈጠረ።የጋዜጦች ሽያጭም ከአንድና ኹለት ሺሕ ተስፈንጥሮ፣ በመቶ ሺሕ ኮፒ ደረሰ፡፡በተለያየ አካባቢ የነበሩ ካድሬዎችም ከሌላ ጊዜ በተሻለ ለተቃዋሚ አባላትና ደጋፊዎች አንጻራዊ የመለሳለስ፣ ሕግና መብቶችን የማክበር ተነሳሽነት አሳዩ። ይህ ግን፣ “ከሕግ ውጭ የሚፈጸሙ ተግባራት አልነበሩም” ማለት ሳይኾን፤ ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር፣ የ97ቱ የፖለቲካ ታሪክ ኮረብታ ኾኖ መታየቱን ያመላክታል ለማለት ነው።የአዲስ አበባ ሕዝብ በከፍተኛ ተስፋ የተሻለ ሥርዐት የሚጠይቅበትን ሥልጡን መንገድ አሳየ። በባህር ዳር እና መሰል ትልልቅ ከተሞች አስደማሚ ሰልፎች እና የአዳራሽ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ተደረጉ፡፡ ትንንሽ ከተሞችም በሰፋፊ ሰልፎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ቻሉ።በጥቅሉ፣ እስከ ምርጫው ድረስ ሁሉም ስብሰባዎችና ሰልፎች እንደ ስማቸው ሰላማዊ ኾነው አለፉ። ግንቦት 7/1997የምርጫው ዕለት፣ ኢሕአዴግ ወኔ ከዳው፤ እንደ ድመት ውጤቱን ቀረጣጥፎ በላው። አስቀድሞ ያሳየው ዴሞክራትነት እንደሚያሸንፍ ተማምኖ እንጂ፣ ሽንፈትን በጸጋ ለመቀበል ተዘጋጅቶ እንዳልነበረም በገሃድ ታየ።በጣም ደማቅ ንጋት መስሎ የጀመረው ምርጫ-97ትም፣ የሐምሌን ጨለማ በሚመስል ኹኔታ ተደመደመ።እዚህ ጋ፣ በድጋሚ ወደኋላ ልመልሳችሁ።እኔ፣ በምርጫ-97 የተወዳደርኩት ደቡብ ጎንደር ከደብረ ታቦር 30 ኪ.ሜ ገባ ብሎ የሚገኝ ክምር ድንጋይ የሚባል አካባቢ ነው፤ ሰፊውን የምርጫ ክልል ገጠሩ ይሸፍናል፤ ከተማዋ አነስተኛና የተወሰነ ዘመናዊ የሚመስል ህይወት ይታይባታል። ከአዲስ አበባ እና ከትላልቆቹ ከተሞች ጋር ባይነጻጸርም፤ ከገጠሩ አንጻር ቆርቆሮ ቤቶች እና የተወሰኑ ሱቆች፣ እንዲሁም ንግድ ያለበት አካባቢ ነው።ቅዳሜ ቅዳሜ ከአራቱም ማዕዘን መግቢያ ወደ ገበያ የሚተምመውን ሰው እያስቆምኩ ነበር፣ የምርጫ ቅስቀሳ የማካሄደው። በራሪ ወረቀት እንሰጣለን፣ የተለያዩ ወኪሎቼም እየተዟዟሩ ይቀሰቅሳሉ። ነዋሪው፣ ከፊቱ ቆመን የምናደርገው ንግግር አልበቃ ስለሚለው፣ ሙሉ ቀን ስናወራ ብንውል አይሰለቸውም ነበር። መሽቶም መሄድ አይፈልግም።አንድ ሰው ሬድዮ ካለው፣ ሌላው ተሰባስቦ ክርክሮችን ሲሰማ ማየት የሚገርም ተነሳሽነት ይፈጥር ነበር። ሕጻናት በየመንገዱ ስናልፍ የቅንጅትን የምርጫ መወዳደሪያ የሁለት ጣት (V) ምልክት በትንንሽ ጣቶቻቸው እያወጡ ያሳዩናል። በየመንገዱ የሚታየው ሁሉ ምርጫና ምርጫ ብቻ ነበር።የምርጫው ዕለትያስለቀሰኝን አንድ አጋጣሚ ላስታውስአካባቢው ተራራማ ስለሆነ፣ የወላጆቼ ቤት ገደል ስር ነው። የገጠር ሰው ብዙ ጊዜ በሥራ ስለሚጠመድ የክት ልብሱን አይለብስም። በተወሰነ ደረጃ ያደፈ ወይም አቧራ የነካው ልብስ ነው የሚለብሰው። የድምጽ መስጫው ቀን ግን፣ ሁሉም ሰው ነጭ ለብሶ ነበር የወጣው። እናም፣ ነጭ ለብሶ በተራራው ላይ በሚገኘው ቀጭን መንገድ ላይ እንደ ነጭ ክር ተዘርግቶ ሲሄድ ስመለከተው፣ በምናቤ ዓድዋ ከዘመተው ወገኔ ጋር አመሳሰልኩት።በርግጥ፣ እንዲህ ተጠራርተው ወደ ዓድዋ የሄዱት ጀግኖች ለዳር ድንበር ሲኾን፤ ይህኛው፣ ዜጎች እውነተኛውን ሉዓላዊ የዴሞክራሲ መብት ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ የዘመቱበት ዕለት ነው።ብቻ ልዩነቱ ባይጠፋኝም፣ ኹኔታው የለቅሶ ሲቃ ፈጥሮብኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ።በሰዐታት ልዩነት፣ የምርጫ ታዛቢዎቻችን በሚኒሻ እና ካድሬ ተደብድበው ለእኔ ሪፖርት ሊያደርጉ ሲመጡ መመልከቴ ደግሞ፣ የፖለቲካው ሰይጣናዊ መልክ ነበር፡፡ በገጠሩ ክፍል ‘ታሪክ ልሠራ ነው’ ብሎ የወጣን ሕዝብ ከእጁ ላይ ካርዱን እየነጠቁና እየደበደቡ ሲመልሱት “እኛ’ኮ ወግ-ማዕረግ አለ ብለን ነው የወጣነው እንጂ፣ እንደ ድሮው ከኾነማ መች እንለፋ ነበር፤” ብሎ አንገቱን ደፍቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ መመልከቱ ቅስም ይሰብራል።የገጠሩን ሕዝብ በግድ ጎትተን ወደ ፖለቲካ አስገባነው እንጂ፣ ከሚኖርበት ጋራ ባሻገር ስላለው ዓለም ለማንሰላሰል ብዙም ጊዜ የለውም። አፈር ቢገፋና አረም ቢያርምም፣ በድንበር ቢጣላና ቢዋደድም፣ ተጋብቶ ቢዋለድም… በዛው በአካባቢው ነው። አልፎ አልፎ፣ ሬድዮ የሚሰሙ ሰዎች ከመኖራቸውም በቀር፣ አብዛኛው በካድሬ ሰንሰለት ተጠፍሮ የታሰረና ድህነቱን ለማሸነፍ የሚሮጥ፣ ቀን-ከሌት የሚለፋ ባተሌ ነው። የከተማው ግን ይለያል።የከተሜነት ህይወት ከተለያዩ ማኀበረሰብና ሃይማኖት ከወጡ ሰዎች ጋር ያስተዋውቃል፤ እውቀትን ያሰፋል፤ የመብትና የመሻሻል ጥማትን ይጨምራል። እንዲሁም፣ የፖለቲከ ጥያቄዎችም ኾኑ በጉና ስሁት ትርክቶች መነሿቸውም መበልጸጊያቸውም ከተማ ነው። ኢሕአዴግ ከበረሃ ያመጣው ትርክት፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከያዘው የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ጋር ይላተማል። እንደ ባህር ተንሰራፍቶ ያለን ሕዝብ አስተስሰብና ታሪክ ከራሱ የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ ብቻ ተነስቶ “ተቀበሉኝ” የሚል ሥርዐት ነበር ያበጀው። ይህም፣ ሕዝቡ መሣሪያ ይዞ ለመዋጋት ባይነሳም፣ በልቡ አቂሞ እንዲኖር አድርጎታል።ጫፍ-ከረገጠው ድህነት በተጨማሪ፤ በመላ ሀገሪቱ በተንሰራፋው ሙስና ካድሬዎች በአጭር ጊዜ ንብረት ሲያፈሩ፣ ብዙ ዓመት የደከመው ለፍቶ-ዐደር ጠብ አይልለትም ነበር። ሕዝባችን ዐቅመ-ቢስ ቢኾንም፣ እነዚህን ቁጭቶች በውስጡ አዝሎ ነው የቆየው። የተጠራቀመው ብሶት ነው፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን በዝረራ እንዲያሸንፍ ያደረገው።በዚያ ምርጫ፣ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት አርከበ እቁባይ ለከተማዋ ከሠሩት አንዳንድ ሥራዎች አንጻር “ይመረጣሉ” የሚል ግምት ነበረኝ። ግና፣ ለዓመታት የተከማቸው ቁጭትና ብሶት፣ ኢሕአዴግን የወከሉትን በሙሉ በጅምላ እንዲሸነፉ አደረጋቸው።በነገራችን ላይ፣ በ1992ቱ ምርጫም፣ ተቃዋሚዎች መከፋፈላቸው በጀው እንጂ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብን ከፍተኛ ድምጽ ያሸነፉት እነርሱ ነበሩ። በጋራ ስላልቆሙ ድምጹ ቢከፋፈልም፣ 68 ከመቶውን ጠቅልለው ወስደዋልና፡፡ ኢሕአዴግ 32 በመቶ አግኝቶ ነው ያሸነፈው፡፡የምርጫው ውጤትየምርጫው ውጤት ከፍተኛ ድል ያገኘንበት ቢኾንም፤ በመጭበርበሩ ምክንያት እኔ የነበርኩበት ቅንጅት “ወደ ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ?” የሚለውን ጉዳይ ከመወሰናችን በፊት፣ በየክፍለ ከተማው ሕዝቡን እየሰበሰብን አወያየን፡፡ በወቅቱ ከተሳታፊዎች የሚነሱት ጥያቄዎችና የትንተና ዐቅምና ጥልቀት ዛሬ ድረስ ይደንቃል። እኛ የሙሉ ጊዜ ፖለቲከኞች፣ ከምንተነትነው በላይ ነበር።በውይይቱ መደምደሚም፣ ሕዝቡ መጀመሪያ ይዞት ከነበረው ትልቅ ተስፋ አኳያ ውጤቱ በመነጠቁ አዝኖ “አትግቡ!” ወደሚል አመዘነ።አሁን ላይ ሳስበው ግን፣ ጉዳዩን ወደ ሕዝብ ከመውሰድ ይልቅ፣ በተሰጠን ድምጽ መሠረት እኛ መወሰን ነበረብን።በርግጥ፣ ሕዝቡን ካወያየን በኋላ፣ የመጨረሻውን ውሳኔ ለሁለት ቀናት ስብሰባ ተቀመጥን ነው የወሰነው።በነገራችን ላይ፣ “ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ?” የሚለው ውይይት አስጨናቂ እንደነበረ ሳልጠቅስ አላልፍም። ምክንያቱም፣ በ60ዎቹ የለውጥ ንቅናቄ ፖለቲካው ሃዲድ በመሳቱ ነው፣ የትውልዱ እጣ-ፋንታ የተበላሸው፤ እኛም የዛ ሰለባ ኾነን የውድቀት አዙሪት ውስጥ የኖርነው። ስለዚህም፣ የምንወስነው ውሳኔ ተመሳሳይ ስህተትና ተመሳሳይ ችግር ፈጥሮ ለትውልድ መከራ እንዳናወርስ የበዛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብን።ነግን በማለም…ኢሕአዴግ ውጤቱን በጠብ-መንጃ መቀልበሱን ተከትሎ፣ ወደ ግጭት ከመግባት፣ “በቀጣይ ሀገራችንን ወደፊት ለማሻገር ምን እናድርግ? ምርጫውን አሸንፈናል፣ ነገር ግን ተነጥቀናል፤ የሚበጀው መንገድ ምንድን ነው?” ብለን ተወያይተን ስናበቃ፣ ወደ ሰባት የሚጠጉ የውሳኔ ሃሳቦችን አሳለፍን።ውሳኔውም፣ ‘ምርጫው ቢጨናገፍም የወደፊቱ ተስፋ እንዳይጨናገፍ ነፃ የኾኑ (እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ መከላከያ ሠራዊት) ተቋማትን ፈጥረን በቀጣይ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ እውን ማድረግ አለብን’ የሚል ነበር።ግና፣ ይህም በበጎ ዐይን ባለመታየቱ፣ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንጋ የድህንነት ሠራተኞቻቸውን አሰማርተው ተከታተሉን፤ ተቋማት በነፃነት መቋቋም አለባቸው ማለታችን ሥርየት እንደሌለው ኀጢአት ተቆጥሮ፣ ከቀናት በኋላ በሀገር ክህደት ተከሰን ታሰርን።ምርጫውን አጭበርብረው እንኳ፣ ለወደፊት በመፍትሄነት ያቀረብናቸውን ሰባት የተቋማት ማሻሻያ ጥያቄዎች ቢቀበሉ ኖሮ፣ የሽግግር ድልድይ መዘርጋት ይቻል ነበር፡፡ ምርጫ-2002ትም ነፃና እውነተኛ ይኾን ነበር።ነፃ ተቋማት በሌሉበት ነፃ ሀገር፣ ነፃ ሕዝብ እና ነፃ ምርጫ ሊኖር አይችልም። ድኀረ-ምርጫበድኀረ-ምርጫው፣ ዐዳዲስ ሕጎች መውጣት ጀመሩ። በተለይ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አባላት አናት-አናታቸውን ተቀጥቅጠው ኮሰመኑ። የፖለቲካ ምህዳሩም ከመቼውም በላይ እንዲጠብ፣ ነፃ ሚዲያውም እንዲዳከም ተፈረደበት፡፡በአጭሩ፣ በድኀረ-ምርጫው ከምዕራቡ ሊብራል ዓለም ጋር ራሱን አቆራኝቶ እርዳታና ብድር ሲያገኝ የነበረው አገዛዝ፣ ሥልጣኑን ሊነጠቅ የሚችልበት ደረጃ ሲደርስ፣ ጭንብሉን አውልቆ እውነተኛ ማንነቱን በይፋ አወጣ። በዚህም ምክንያት፣ ምርጫ-2002 እጅጉን በከፋ አፈና ውስጥ ተካሄደ። ምርጫ የሕዝብ ሉዓላዊ መብት የሚከበርበት ሳይኾን፣ አገዛዞች ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል የሚጫወቱበት ተውኔት ተደረገ። የኢሕአዴግ ሰዎችም ጥሩ ተዋናይ ከመኾናቸው በዘለለ፤ ለራሳቸውም ለሀገርም ክብር የሌላቸው፣ ለትውልድም ተስፋ የሚሰጥ ነገር ለመሥራት አለመዘጋጀታቸውን አረጋገጡ።በርግጥ፣ ጭቆና እስካለ ድረስ ትግል አይቆምምና፣ ትግሉ ቀጠለ፡፡ ሕዝብን ጸጥ ለማሰኘት ከ1998 ዓ.ም በኋላ በወጡት አፋኝ ሕጎች እስሩ በገፍ ተጧጧፈ፤ (በተለይ በፀረ-ሽብር እና በፕሬስ ሕጉ።) ይሁንና፣ ነፃነት በሌለበት ሀገር በሞትና በህይወት መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ በመኾኑ፣ ሕዝቡ የተቃውሞ ትግሉን አፋፋመ። የምርጫው ውጤትና ምስቅልቅልአምባ-ገነኖች ፈሪዎች ናቸው፣ ፍርሃት ደግሞ ጨካኝ ያደርጋል።የሚፈራው ነገር ያለ አካል፣ “እገደላለኹ” ወይም “እሞታለሁ” ብሎ ያስባል እንጂ፤ በጋራ ሊያመጣ የሚችለው ለሁሉም የሚበጅ መውጫ መንገድ አይታየውም። የነገሮች ሁሉ ማጠንጠኛ “እኔ ነኝ” ብሎ ስለሚያምንም፣ ሥልጣን ማጣት የዓለም መጨረሻ ይመስለዋል።የ1997ቱ ምርጫ ከተበላሸ በኋላ፣ ይህ ነው የኾነው፡፡ ሰኔ 1/1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች “የአርሶ ዐደር ወላጆቻችን ድምጽ ይከበር!” የሚል የተቃውሞ ሰልፍ በስድስት ኪሎው ካምፓስ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢ ለሦስት ቀናት በርካታ ግድያዎች በአገዛዙ ጸጥታ ኃይሎች ተፈጸሙ።የዚህ ዘግናኝ ግድያ ዓላማ ስሌቱ፣ ‘ሕዝብ በፍርሃት ሲርድ፣ እኛ እንደፈለግን እንገዛዋለን’ ነበር። ግና፣ ጭቆና እስካለ ድረስ፣ ሕዝብ ስልት ሊቀይር ወይም እስኪብስበት ሊጠብቅ ወይም “ይሻሻላል” ብሎ ተስፋ ሊያደርግ ይችላል እንጂ፣ እስከ መጨረሻው ዝም አይልም። ስለዚህም፣ በድኅረ-ምርጫው ኢሕአዴግ የከተማውን ነዋሪ በደዴሳ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በዝዋይ እና በሌሎች እስር ቤቶች አፍሶ ቢያስርም፤ ነብዩ የተባለ የ10 ዓመት ልጅን ጨምሮ፣ አያሌ ወጣቶችን በጭካኔ ቢገድልም፣ ተቃውሞው አልበረደም። የሕዝቡም እምቢተኝነት አልቀነሰም።በተቃራኒው፣ ኢሕአዴግ፣ በዚህ አሰቃቂ ድርጊቱ ከሕዝብ ጋር ላይመለስ ተቃቃረ። እስከ መጨረሻው ግበአተ-መሬቱም ድረስ በጉልበቱ ቀጠለ እንጂ፣ ቅቡልነትን አላገኘም።በወቅቱ፣ በቀላሉ ማስተካከል የሚቻሉ ነገሮችን አበለሻሽቶ፣ ኢትዮጵያን ዛሬ ላለችበት ምስቅልቅል ሁኔታና ቀውስ ዳርጓት አለፈ። ብዙ ጥያቄዎችም ሳይመለሱ ቀሩ።ከየካቲት እስከ መጋቢትከ66ቱ የየካቲት አብዮት፣ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሥልጣን እስከያዙበት የ2010ሩ ወርሃ መጋቢት ድረስ (ለሰባ የጥምዝዮሽ ዐመታት) ኢትዮጵያውያን ያነሷቸው ጥያቄዎች ጠቅለል ተደርገው ሲቀርቡ፡- የብሔር እኩልነት፣ የመሬት ፍትሃዊ ክፍፍል እና ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም የሚሉ እንደነበረ ይታወቃል፤ (እነዚህ ጥያቄዎች በ97ቱም ምርጫ በዋንኛነት ክርክር እንደተደረገባቸው ልብ ይሏል፡፡)በእኔ ግምገማ፣ ሦስቱም ጥያቄዎች ዛሬም አልተመለሱም። ሕዝባዊውን ንቅናቄ ጠልፎ የንጉሠ-ነገሥቱን ዙፋን የወረሰው ደርግ፣ በተወሰነ መልኩ የመሬት ጥያቄን ለመመለስ የሄደበት ሙከራ ቢኖርም፤ ‘ጥያቄው በትክክለኛው መንገድ ተመልሶ ነበር ወይ?’ ከተባለ፣ ሕዝቡን የንብረቱና የሀገሩ ባለቤት ማድረግ ስላልቻለ “ፈጽሞ” የሚል ነው ምላሹ።የብሔር ጥያቄውንም፣ ኢሕአዴግ ለሥልጣን መጠቀሚ ከማዋሉ በዘለለ፤ በተለያዩ ማኀበረሰብ መሃል የጥል ግድግዳ እንዲኾንና አንድነት እንዲነወር ነው ያደረገበት።ሕዝባዊ መንግሥትን የተመለከተው ጥያቄማ፣ ለአፋዊነት እንኳ ሳይሞከር ነው የተደፈቀው።በርግጥ፣ ዴሞክራሲያዊ ወይም ሕዝባዊ መንግሥት ሊመሠረት የሚችለው ሉዓላዊ የኾነ ሕዝብ ሲኖር ነው። የሉዓላዊ ሕዝብ መሠረቱ ሉዓላዊ ግለሰብ ነው። አንድ ሉዓላዊ ግለሰብ፡- ባመነበት ሃሳብ የመደራጀት፣ የመሰለፍ፣ የመጻፍ፣ የመናገር፣ ንብረት የማፍራት፣ በነፃነትና በህይወት የመኖር መብቶቹ ተፈጥሯዊ ናቸው፡፡ እነዚህ የተገመዱ መብቶች በምልዓት ሲከበሩ ነው፣ ነፃ ግለሰብና ማኅበረሰብ መፍጠር የሚቻለው።በጣም የሚያስደነግጠው ደግሞ፣ እነዚህ ጥያቄዎች ሳይመለሱ፣ በተለይ ባለፉት ሰባት ዓመት በርካታ ዐዳዲስ ጥያቄዎች እየተፈጠሩ መቀጠላቸው ነው። “ከ1997ቱ ይበልጥ የጎዳኝ የ2010ሩ ለውጥ ክሽፈት ነው” አስታውሳለኹ፣ መጀመሪያ ለእስር የተዳረኩት በምርጫ-97 በቅንጅት ለኹለት ዓመት ገደማ ነው። በአንድነት ፓርቲ ደግሞ፣ በ2004 ዓ.ም ከመስከረም ወር ጀምሮ ለስድስት ዓመት ተኩል ታሰርኩ። እነዚህ እስሮች ሲደመሩ፣ ባለፈው ሳምንት 17 ዓመት ሞላው ያልኳችሁ ልጄ፣ የህይወቱ ግማሽ ያህል ናቸው።እዚህ ጋ፣ ሳልጠቅሰው ማለፍ የማይቻለኝ፣ በአዘቦታዊው አነጋገር “ለሀገር ብለን፣ ለወገን ብለን ነው የምንንገላታው” እንበል እንጂ፤ ማንም ሰው የሚታገለውም ዋጋ የሚከፍለውም ለራሱ ብሎ መኾኑ ነው። እኔም፣ ከዚህ አንጻር፣ ለራሴ ነው የታገልኹት።ይሁንና፣ በግለሰብ ተነሳሽነት የሚደረጉ ጥረቶች፣ ከሌሎች ጋር ሲገጣጠሙ ለሀገር የሚተርፍ ነገር የመምጣታቸው አይቀሬነት አይስተባበልም። መነሻው ግን፣ ግለሰብ ሁሌም የራሱን ጥያቄ ለመመለስ በሚያደርገው ትግል የሚመጣ መኾኑ ነው።በጥቅሉ፣ ምርጫ-97 በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍ ብሎ የሚታይ ቢኾንም፤ ለእኔ ከህይወቴ ጋር ተቆራኝቶና ቅርቤ ኾኖ የሚሰማኝ፣ በድጋሚ በ2010 ዓ.ም የተጨናገፈው ለውጥ ነው።ያ ሁሉ መከራና ክፉ ዘመን አልፎ በዐዲስ ንጋት፣ የአንድ ሀገር ልጆች እየተመካከርን የምንሠራበት ዘመን መጣ ብዬ የእውነትም ተስፋ አድርጌ ነበር። ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ሊመለስ ነው’ የሚል ግምትም ነበረኝ። በቅርጹም ኾነ በይዘቱ ከ97ቱ ፈጽሞ ስለሚለይም፣ በሁላችንም ዘንድ ተስፋ ማሳደሩ የሚጠበቅ ነበር። ብቻ፣ የቅርብ ጊዜም ስለኾነ ነው መሰለኝ፣ ለስሜቴ የሚቀርበው የ2010ሩ ክሽፈት ነው።ሀገር በቀል ፖለቲካ ሲባልጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከሚያነሷቸው ሃሳቦች መካከል አንዱ “ሀገር በቀል የፖለቲካ ባህል አልፈጠርንም” የሚለው ወቀሳ ነው። ግና፣ “መስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር ድንጋይ አይወረውርም” እንዲሉ፤ ይህን መሰሉ አነጋገር ከእሳቸው ሲመጣ ወለፈንዲ መኾኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም፣ የብልጽግና “ወንጌል” ራሱ ከኢትዮጵያ ነባርና ሀገር በቀል ፖለቲካ እሳቤ የተቀዳ አይደለምና፡፡የሀገር ባህል እና ቅርስ እያጠፉ “ቤት” ማለት ፎቅ ብቻ የሚመስላቸው፣ ከተሞችን በመብራቶችና በብልጭልጭ ነገሮች ማጥለቅለቅን አንደ ስልጣኔ ማየታቸውም ጮኾ የሚነግረን አንድ እውነታ፣ የዶ/ር ዐቢይ መንገድ “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ” ዐይነት መኾኑን ብቻ ነው፡፡ከዚህ ባለፈ፣ “ሀገር በቀሉ ሃሳብ ላይ አልሠራንም” የሚሉት ነገር ተራ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ዛሬስ…?ካርል ማርክስ “ታሪክ ራሱን ይደግማል፤ መጀመሪያ አሳዛኝ፣ ቀጥሎ ቧልታዊ በኾነ መንገድ” እንዲል፤ ዛሬም የትላንቱ እየተደገመ ነው።ይህ ባይኾንማ ኖሮ፣ ኢትዮጵያችን ለሁለተኛው የዓድዋ ድል ክብር በበቃች ነበር። ዓድዋ ሙሉ የሚኾነው ከዳር ድንበር አልፈን፣ ሕዝባችን ነፃነት ሲኖረው ነው። በዓድዋ ጦርነት ከደከሙና ከቆሰሉ ሰዎች አብዛኛዎቹ ወደ ቀዬቸው ሲመለሱ ነፃነት አልነበራቸውም። በየአካባቢው ያሉ የጌቶቻቸው ባሪያዎች፣ አገልጋይና ገባር ነበሩ።ለዚህም ነው፣ ‘ሰው ነፃ ባልኾነበት ሀገር፣ የዳር ድንበር ነፃነት ብቻውን ትርጉም አይሰጥም’ ብዬ በጽኑ የማምነው።ግለሰብ በሀገሩ የመብቱና የነፃነቱ ባለቤት የሚኾንበት መንገድ በ1966ቱ አብዮት ብልጭ ብሎ ድርግም አለ፡፡ በ1997 ዓ.ም ደግሞ ከዛኛውም በላቀ ደረጃ በዴሞክራሲያው መንገድ ተጀምሮ፣ በኢሕአዴግ ወጥ አምባ-ገነንነት በጅምር ቀረ።እንዴት ያለ ኪሳራ ነው?አሁንም የወደቅንበት አዘቅት ከዛው የሚመዘዝ ነው።አስቀድሞ እንዳነሳኹት፣ በእኔ ዕይታ፣ በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ነፃ የፖለቲካ ተቋማትን መገንባት አለመቻሉ ነው። ሁሌም ተቋማት ሲገነቡ፣ ሥርዐቱ በፈለገው መጠን ለመዘወር እንዲያመቸው፣ ቁመታቸው ከገዥዎች በታች እንዲኾኑ ተደርገው ነው። እንዲህ ዐይነት ተቋማት ደግሞ፡- አምባ-ገነኖችን መቅጣት፣ መገሰጽና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕግ ፊት እኩል የሚሆንበትን ሥርዐት የመገንባት ዐቅም አይኖራቸውም። በእነሱም፣ ትክክለኝ የዴሞክራሲ ሽግግር ማምጣት አይቻለም።ሕዝባዊ መንግሥት የሚዋለደው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእውነት ቁጭ ብለው መነጋገር ሲችሉ ብቻ ነው። መለስ ብለን ስናስተውል፣ አቶ መለስ ዜናዊ ያ እድል ነበራቸው። በግሌ ሙት መውቀስ አግባብ ነው ብዬ ባላምንም፤ እሳቸው ያጠመቋቸው ካድሬዎችን ዝም ብለው ከለቀቋቸው፣ ሀገሪቱን ምን ዐይነት ቅርቃር ውስጥ ይዘዋት እንደሚገቡ የመረዳት ዐቅሙ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን፣ ቀናነት በማጣት ‘ኢትዮጵያ በካድሬዎች እጅ ወድቃ ድራሿ ቢጠፋም ይጥፋ!’ ብለው በመፍረዳቸው፣ አሁናዊው ሁኔታ ተከስቷል። እርሳቸውም በታሪክ ታላቅ የሚባሉበትን እድል አምክነዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም፣ የሰው አስተያየት ለመስማት በጎ ፈቃድ እንደሌላቸው በሚገባ ይታውቃል። በዚህ ላይ፣ ፓርቲያቸው ውስጥ ከሚቀላቅሏቸው አመራሮች የሚበዙት ከፖለቲካ የሚገኘውን ሥልጣንና ጥቅም የሚያሰሉ እንጂ፤ ፖለቲካ ውስጥ ኃላፊነት፣ ተጠያቂነትና ግዴታ መኖሩን የተረዱ አይመስለኛም፡፡ይህም ኾኖ፣ ዶ/ር ዐቢይ፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ስህተት ቢማሩ፣ ወደፊት ታሪክ መሥራት የሚችሉበት እድል አሁንም አላቸው፡፡በተረፈ፣ ታላቅ መኾንን ሁሉም ሰው ይፈልገዋል፤ ጥያቄው ‘ምን ዐይነት ታላቅነት?’ የሚለው ነው፡፡ እንደ አዶልፍ ሂትለር እና እንደ መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ወይስ እንደ ማሕተመ ጋንዲ እና ኒልሰን ማንዴላ?ምላሹ እንደ እነ-ጋንዲ ከኾነ፣ ዝቅ ብሎና ራስን ከንግሥና አውርዶ፣ ኢትዮጵያን በማስቀደም ከሁሉም ወገኖች ጋር ተቀምጦ፣ ሀገሪቱን ወደ የት እንውሰዳት? የሚለው ላይ በሃቀኝነት መነጋገርና መደራደር ያስፈልጋል። ይህ ባልኾነበት ሁኔታ ለሚመጡት 20 ዓመታትም ተስፋ ማየት ይከብዳል። ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ዐውድ ተስፋ አስቆራጭ ነው። በዘመኗም በዚህ መጠን ወድቃ አታውቅም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል።በበኩሌ፣ እንደ ግለሰብ ተስፋ የማደርገው፣ እግዚአብሔር ረድቶን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ቁጭ ብለው ከዚህ በፊት ያልታየ እውነተኛ ሰጥቶ መቀበል የሚኖርበት የድርድር እድል እንዲመጣ ነው። በዚህም፣ አንድ የጋራ ባለ-አደራ መንግሥት ተቋቁሞ፣ ሀገራችንን አሻግረን እንደ ትውልድ ከወደቅንበት የምንነሳበት በጎ አዙሪት ማስጀመር ከቻልን፣ እሽክርክሪቱ እየቀጠለ ሀገሪቱን ወደ ዋሻው ብርሃን ጫፍ መውሰድ ይቻላል ብዬ አምናለኹ።ኢትዮጵያን እስከ ዛሬ ገምዶ ያቆየው የሕዝቡ አንድነት፣ ሃይምኖት፣ ባህልና መከባበር ጊዜ በሄደ ቁጥር እየተሸረሸረ ነው።በጥቅሉ፣ ፈጣሪ ልቦና ሰጥቷቸው ጀግንነትና ወኔ ሰንቀው፣ ሸፍጥና ሃኬት በሌለበት እውነተኛ ሰጥቶ በመቀበል ድርድር የአደራ መንግሥት ከተቋቋመ እና ነፃ ተቋማት በመመሥረት ተአማኒ ምርጫ ከተካሄደ ሀገሪቱ ወደ ትክክለኛ ሂደት ውስጥ የምትገባበት እድል ይፈጠራል።
By Godana
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት፥ ጥናት እና ምርምር ካላቸው የአስርት ዓመታት ልምድ በተጨማሪ፣ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ቆይተዋል። በተለይም በ 1990ዎቹ መጀመሪያ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በተሰኘው ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ አመራር ነበሩ። በአሁኑ ወቅትም የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀ መንበር ናቸው።መረራ የቀድሞው ፓርቲያቸው ኦብኮ፥ ብሎም ኦብኮ አባል የነበረበት ሕብረት የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የተሳተፈበትን እና እኛም በዚህ ልዩ ዕትማችን ልንዳስሰው ያነሳነውን ምርጨ-97ን ወደ ኋላ ዘወር ብለው በጽሑፋቸው ቃኝተዉታል። በመጣጥፉ፥ የምርጫ-97ን ታሪክ አሁን ኢትዮጵያ እያለፈችበት ካለው ብሎም ከነገ ጋር በማስተያየት አካፍለውናል።ለጽሑፋቸው ማጀቢያም የሃጫሉን አንድ ረጋ ያለ ሙዚቃ ምረጡልኝ ባሉት መሰረት፣ እኛም ሃጫሉ ሁንዴሳ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ለሕዝብ ከደረሰው “ማል ማሊሳ” አልበሙ “ኩሌ ኮ” የተሰኘውን መርጠንላችኋል።ቢጫውን ምልክት በመጫን የሙዚቃ ምርጫውን ከመጣጥፉ ጋር ታጣጥሙ፥ ብሎም በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ካለዎት ያካፍሉን ዘንድ እንጋብዛለን። ጎዳናበኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምርጫ መካሄድ የጀመረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን የተቀረፀውን ሕገመንግሥትን ተከተሎ ነበር።ታዲያ ከዘውዳዊው ስርአት ጀምሮ እስከዛሬ ባሉት ከ 70 በላይ ዓመታት የተካሄዱ ምርጫዎች በ1997 ዓ.ም ከተካሄደው ምርጫ ጋር ሲወዳደሩ - ሁሌም እንደምለው - አንዳቸውም እንኳን ለምርጫ ለ’ቅርጫ’ እንኳ የማይቀርቡ ነበሩ።በተለይም ከ 1997 በፊት የነበሩት ይቅር እና ለዴሞክራሲ ባህል ጅማሮ፤ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ አላደረጉም።ታዲያ ይህንን የታሪክ መስመር የቀየረ ሊባል የሚችለው ምርጫ-97 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስከ አሁን ከተካሄዱ ምርጫዎች፤ ከቅርጫ ያለፈ፥ ምርጫ የሚመስል፣ ፓርላማውም የሀገር ፓርላማ የመሰለ መልክ ሊይዝ የተቃረበበት ነበር።ይህ ክስተት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለዴሞክራሲ ጅማሮ በር ከፋች ነው ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነበር።አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ወዲህ እና ከ1997 በፊት ተካሂዶ እኛም እንደ ፓርቲ የተሳተፍንበት የ 1992ቱ ምርጫ፥ ሙከራ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝበች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች መልክ ይዘው የወጡበት አልነበረም።እንደውም ምርጫ ውስጥ ገብቶ ኢሕአዴግን ከመግፋት ይልቅ ምርጫውን በማውገዝ ራስን ማግለል ተቃዋሚዎች የሚከተሉት የተለመደ አካሄድ ነበር።በምርጫ-92 በተለይም ከሀዲያ አካባቢ ተቃዋሚዎች በንፅፅር ጠንካራ ውድድር ቢያደረጉም በ1997 ከታየው የተቃዋሚዎች ተሳትፎ ጋር ሲተያይ መቀራረቡ ቀርቶ በአንድ ሚዛን የሚለካ አልነበረም።የ 1997ን ምርጫ ከቀደሙት ምን ለየው?ምርጫውን ምርጫ ካስመሰሉት ዋና ቀለሞች አንዱ ሚሊዮኖች በኢትዮጵያ ምድር ከዳር እስከ ዳር ተንቀሳቅሰው “ድምጻችን ዋጋ አለው” ብለው ወደ ተሳትፎ የገቡበት መሆኑ ነው።ከምርጫው አስቀድሞ የኢሕአዴግ አመራሮች ግምት ሕዝቡ የቱንም ያህል ወጥቶ ቢሳተፍ አብዛኛው ተቃዋሚ ትኩረቱ ከተሞች አካባቢ በመሆኑ፤ በአንጻሩ ‘ኢሕአዴግ የገበሬው መንግሥት በመሆኑ እና ሰፊ የአርሶ አደሩ ድጋፍ አለን’ የሚል ግምገማ ነበራቸው። ‘ተቃዋሚዎች አንዳንድ ከተሞችን ቢያሸንፉም ገጠሩ የኢትዮጵያ አካባቢ ላይ ያለን የሕዝብ ድጋፍ የበላይነት ለአጠቃላይ አሸናፊነት ያበቃናል’ የሚል ሙሉ ድምዳሜም ይዘው ነበር።ኢሕአዴግ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በወቅቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ከፈት አድርጎት ነበር።ለዚህ እንደ ትልቅ ማሳያ የሆነው እና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቀው በመንግሥት የመገናኛ ዘዴዎች በቀጥታ ሲተላለፍ የቆየው የፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ነው። ያ ከ ምርጫ-97 በኋላም ቢሆን እስከዛሬ ተደርጎ አያውቅም።ከከተማው፥ ከሊሂቃኑ እና ከወጣቱ አልፎ የገበሬውንም ልብ ሳይቀር የሳበ ክርክር ነበር።በተለይም ሦስቱ ዋነኛ ተፎካካሪ ጥምረቶች - ማለትም ኢሕአዴግ በአንድ በኩል ቅንጅት አና ኅብረት በሌላ በኩል ያደረግናቸው ክርክሮች እስከ ዛሬ ድረስ ከ20 ዓመታት በኋላ አልፎ አልፎ ሲነሱና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲጋሩ በግሌ አስተውያለኹ።ስለምርጫው ሳስብ በአዕምሮዬ ከሚከሰቱ ምስሎች አንዱ የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ በተለያዩ የገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍሎች በምንቀሳቀስበት ወቅት የማየው አርሶ አደር ነበር።ገበሬው እርሻውን እያረሰ ማሳው ላይ ሆኖ ራዲዮውን አንግቶ ሲያዳምጥ መመልከት የተለመደ ነበር። ምርጫው ለየት ባለ መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ልዩ የተስፋ ስሜት ፈጥሮ ነው የሄደው።በእርግጥም በሰዓቱ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚመስል ነገር ሙከራ ነበር። ሆኖም ኢሕአዴግ ለሥልጣን በነበረው ስስት የተነሳ፥ ለራሱም ለሁላችንም ያልሆነ የተጨናገፈ ሽግግር ፈጥሮ አለፈ።ስለዚህም ነው የ97ቱ ምርጫ ከአብዮቱ ብሎም ከሽግግር መንግሥቱ መክሸፍ በኋላ በድጋሚ የተጨናገፈ ትልቁ እድል (Grand Failure) ነው ብዬ የማምነው።በእርግጥ ከ 1997 በኋላ በነበሩ ዓመታት፥ ውድቀቶች እና ያመለጡ እድሎች ጨመሩ እንጂ አልቀነሱም።ቅድመ ምርጫው ላይ የታየው ተስፋ ከምርጫው ዕለት ጀምሮ መክሰም ሲጀምር ዋና የትኩረት ስበት የነበረችው አዲስ አበባ ለዚህ መገለጫ ነበረች።በተለይም ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፋቸው ገዢው ፓርቲ ላይ የፈጠረው ድንጋጤ ቀላል የሚባል አልነበረም።ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ላይ የገጠመው ሽንፈት ከመዲናዋ አልፎ ውጤቱ በመላው አገሪቱ ላይ ለተወሰደው እርምጃ ምክንያት ሆነ።የአዲስ አበባ ውጤት ሲመጣ የገዢው ፓርቲ ሰዎች መደናገጣቸውን ተከትሎ፥ በዛው በምርጫው ዕለት ማታ አቶ መለስ ዜናዊ በተለይም ካድሬውን ለማረጋጋት ሲሉ 50 በመቶ እንኳ የሕዝብ ድምፅ ተቆጥሮ ሳያልቅ “አዲስ አበባ ላይ ኢሕአዴግ ተሸንፏል፣ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግን አሸንፏል” የሚል መግለጫ ሰጡ።ከዚያም በሰፊው የምርጫ ድምፅ የማስተካከል ተግባር ውስጥ ተሰማሩ። የሚችሉትን ያህል አስተካከሉ። አንዳንድ የፈሩባቸው ቦታዎችን ሲለቁ፥ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ድምፅ ወደ ማሰረቁ ከዛም አልፎ በተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫው እንደገና እንዲደገም አደረጉ።በዚህ እንደ ምሳሌ የሚነሳው አቶ አባ ዱላ ገመዳ የተወዳደሩበት አካባቢ፤ ምርጫው ያለአግባብ እንዲደገም ብሎም ኮሮጆ ፊት ለፊት እንዲሰረቅ ተደርጎ ነው እንዲያሸንፉ የተደረገው። እንዲህ ባሉ ስልቶች የተሸነፉባቸውን ቦታዎችን መልሶ ለመያዝ ሁኔታዎችን አመቻቹ።ይህንና ተያያዥ ክስና ቅሬታዎችን በተመለከተ፥ በተቃዋሚዎች በኩል ወደ 299 የቅሬታ ነጥቦችን ለምርጫ ቦርድ አቅርበን ነበር።ከምርጫው በፊት ምርጫ ቦርድም ሆነ ኢሕአዴግም ፈሪሃ እግዚአብሔር እንኳ ባይሆን እንኳ ትንሽ የማፈር አዝማሚያ ይታይባቸው ነበር። ኋላ ላይ ግን ሥልጣን የማጣቱ ጉዳይ ዐይኑን አፍጦ ሲመጣ፥ ይሉኝታንም ትተው ፊት ለፊት የሕዝብ ድምጽ ቆጠራውን የማበላሸቱን ሥራ ገፉበት።በአንፃሩ ቅንጅትና ኅብረት ምርጫ ቦርድ ላቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ያቀረቡት የድምፅ መጭበርበር ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሲደረግ፥ 30 የሚሆኑ ኢሕአዴግ ያቀረባቸው ቅሬታዎች ግን ተቀባይነት አግኝተው ዳግም ምርጫ [በአንዳንድ አካባቢዎች] እንዲካሄድ ተወሰነ።በኢትዮጵያ ምድር - በ ሦስት ሺህም ይሁን 150 ዓመታት ታሪካችን - ለመጀመሪያ ግዜ ምርጫ የሚመስለውን የተለየ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር የነበረንን እድል እና ተስፋ ኢሕአዴግ አጨናገፈው።በዚያም ውሎ አድሮ ሁላችንም ከስረንበታል።ምንአልባትም ከእኛ የበለጠ የኢሕአዴግ መሪዎች ዋጋ ከፍለዉበታል።ለተስፋው መጨንገፍ - የተቃዋሚዎች ድርሻእንደሚታወቀው በጊዜው ሁለት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስብስቦች ነበሩ፥ አንደኛው ኅብረት እና ሌላኛው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ።በወቅቱ የእኔ ፓርቲ አባል የነበረበት ኅብረት በተወሰነ ደረጃ የፖለቲካ ሜዳውን ለማመቻቸት ከምርጫው ቀደም ብሎ ከኢሕአዴግ ጋር ተደራድሮ ነበር። ያም ድርድር በተወሰነ ደረጃ ምርጫው ከቅርጫ የተሻለ እንዲሆን አስችሎታል።ምንአልባትም ቅንጅትና ኅብረት አንድ ላይ ሳንለያይ ቆመን ቢሆን ኖሮ ወይ ተሰባስበን ወይፓርላማ ወይ እስር ቤት እንገባ ነበር።ነገር ግን ያ እድል አመለጠን።ቅንጅቶች እስር ቤት ገቡ፣ እኛ ፓርላማ ገባን።ግን የሁለታችንም እድል የተሻለ ሊሆን አልቻለም።የፓርቲዎቹ ክፍፍል መነሻ፥ በእኔ እምነት፥ ከሁሉም ይልቅ የዳያስፖራው ግፊት ነው። ዳያስፖራው የቅንጅት መሪዎችን ከጠበቅነው/ከምንገምተው በላይ የገፋቸው ይመስለኛል።“ከነ’እገሌ ጋር እንዴት ትሰለፋላችሁ” ይሏቸው ነበር። ኅብረት ውስጥ ከነበሩት የመኢሶን እና ኢሕአፓ አባል ከነበሩ ጋር ለምን ተቀናጃችሁ የሚል ሰፊ ግፊት እንደነበር ይታወቃል።ቅንጅት እና ኅብረት መካከል በተለይም የቅንጅት አመራሮች በተወሰነ ደረጃ የማይፈልጓቸው የብሔር ንቅናቄዎችም ኅብረት ውስጥ ከመኖራቸው በቀር፥ እምብዛም የሚለየን አቋም አልነበረም።ያም ሆነ ይህ፥ በሁለት ብንከፈልም ኢሕአዴግን አሸንፈናል።ፖለቲካን እንደሸቀጥ - ምርጫ 1997 የወለደው አዲስ ባህልኢሕአዴግ ከምርጫው በኋላ በተለይም በጉልበት - ማለትም የወታደር ኃይል መጠቀሙን እና የፖለቲካ ምህዳሩን ሙሉ ለሙሉ ለማፈን መንቀሳቀስን መረጠ። ከዚህ እኩል የተጠቀመው መንገድ ገንዘብን በመጠቀም ፓርቲዎችን ከውስጥ መከፋፈል ነበር።እናም በጣምራ ጣልቃ ገብነት - (Militarization of Politics and Commercialization of Politics) - በቀጥታ ሥራ ላይ ወደማዋል ተሻገረ። ፖለቲካ ሸቀጥ ሆነ። ሌላኛው ዘዴ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ፈጥሮ እና አደራጅቶ ማሰማራት ነበር።የዚህ ዘመቻ ሰለባ ከነበሩት መካከል አንዱ የእኛ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) እና ቅንጅት ይገኙበታል።በአደባባይ ፖለቲካ ሸቀጥ ሆኖ ከፖለቲካ ፓርቲ እየወጡ ራሳቸውን የሚሸጡና የሚለውጡ ሰዎች መታየት ጀመሩ። ጉልበትና ኃይል መጠቀሙ ድሮም የነበረ ቢሆንም፥ የፖለቲካ ንግዱ ግን ተጨማሪ አዲስ ነገር ሆነ።ይህ በእርግጥ አሁንም በስፋት ሲደረግ እያየን ያለነው ነገር ነው፥ ነገር ግን ባህሉ ከ ምርጫ 1997 ማግስት የጀመረ ነው። “ፓርላማ እንግባ አንግባ”ወደኋላ መለስ ስንል፥ በምርጫ 97 ታዛቢዎች የተሻለ ሚና ነበራቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ዳግም ምርጫ ሲካሄድ ግን፥ እኛም ቅንጅትም “ሰዉን እናስጨርሳለን” ብለን ከምርጫው ጥለን ወጣን።በሰዓቱ ኢሕአዴግ ጠመንጃውን ወድሮ ነበር የወጣው። አስቀድሞ የነበረው ትንሽ የመፍራትም፥ በርከት ብለው የነበሩ የውጭ ታዛቢዎችን ዐይቶ የማፈሩም ነገር በኋላ ላይ ጠፍቶ ነበር። በምርጫው መሸነፋቸውን እርግጠኛ ሲሆኑና ሁኔታውን ሲረዱ፥ ጠመንጃ ይዘው ወጡ።ያለተወዳዳሪም 30 የሚጠጉ ቀደም ብሎ ተቃዋሚዎች ያሸነፏቸውን መቀመጫዎችን መልሰው ወሰዱ።ከዚያ ጎን ለጎን በቅንጅት በኩል ፓርላማ እንግባ አንግባ የሚለው ሙግት በድኅረ ምርጫው አንኳር ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ነው።እኔ በግሌ ከቅንጅት ዋና ኃላፊዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግሬ ያለኝን ፅኑ አቋምም ገልጬ ነበር።“እኛ ባለንበት ሁኔታና አቅም መንግሥትን በጉልበት ከሥልጣን ለማውረድ የምንችል ስላልሆነ፥ ትግሉን ከውስጥም ከውጭም እንቀጥል” የሚል ሐሳብ አቀረብኩ።ይህ ለቅንጅት ያቀረብኩት ምክር ብቻ ሳይሆን እኔ የነበርኩበት ፓርቲ ኦብኮ ብሎም ኅብረቱ የወሰደው እርምጃ ነበር።ነገር ግን እዚህ ላይ ሳላነሳ የማላልፈው ጉዳይ፥ በፓርላማ የቅንጅት አባላት እንዲከሰሱ ያለመከሰስ መብታቸው ሲነሳ፥ እኛ ፓርላማ ረግጠን ወጥተናል።ያ እርምጃ ምን አልባትም በኢትዮጵያ የፓርላማ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያም እስካሁንም ያልተደገመ ሳይሆን አይቀርም።ረግጠን ከመውጣታችን በፊትም “ድምጽ መከልከል ብቻ ሳይሆን አሸንፈናል ብላችሁ የጉልበት ሥራ መሥራት የለባችሁም” ብለን ተቃውሟችንን በግልፅ ተናግረናል። የዴሞክራሲ ጭምብሉ ሲወልቅ ኃይልና ጉልበት ወደ መጠቀም የዞረው ኢሕአዴግ፥ አዲስ አበባ፣ አማራ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች አፈና እና ግድያ ይፈጽም ነበር። በፖለቲካ ተሳታፊ የነበሩ ተወዳዳሪዎቻችንን ሳይቀር መገደላቸውን እና ድብደባ መፈፀሙን ተከትሎ፥ ጉዳዩ ይጣራልን ብለን ከኢሕአዴግ ጋር ተደራድረን አጣሪ ኮሚሽን ጭምር ተቋቁሞ ነበር።የማጣራቱ ውጤት ለጥፋቱ ተጠያቂ መንግሥት ነው የሚል ግኝት ሲያሳይ፥ ሰነዱ እንዲጠፋ ብሎም እርማት እንዲደረግበት ተደረገ። በፈጠራ የተዘጋጀው ሪፖርት ኋላ ላይ ለፓርላማ ሲቀርብ ‘መንግሥት አላስፈላጊ እርምጃ አልወሰደም’ የሚል ግኝት ተሰጥቶት ከመጀመሪያው የኮሚሽኑ ሃቀኛ ግኝት ጋር የሚቃረን ይዘት ይዞ ቀረበ።የምርጫው ቁርሾ እና እርሾከምርጫ - 97 በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በተለይ በወጣቱ ዘንድ የተሻለ የመሰባሰብ ምልክቶች የታየበት ግዜ ነበር።ነገር ግን ኢሕአዴግ ከምርጫው በኋላ ጠብመንጃ የተጠቀመውን ያህል የመከፋፈል ፖለቲካንም እንዲሁ ተጠቅሟል።በተለይም በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን እምነት በመሸርሸር፣ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር በማድረግ ከፋፍሎ የመግዛት ፖለቲካ ጎልቶ ታይቷል።ምንም እንኳ ይህ ድርጊት ከዚያ ቀድሞ በነበረው ዘመን የነበረ ቢሆንም፥ ማኅበረሰቦችን እርስ በርስ የማጋጨት የፖለቲካ አሠራር በዋናነት በሥራ ላይ የዋለው በኢሕአዴግ ነው፥ አሁንም በተለያየ ደረጃ ቀጥሏል።ይህም ብዙ ነገር አበላሽቷል፤ ምናልባትም በወቅቱ ከተሠሩ ትልቅ ታሪካዊ ስህተቶች አንዱ ሆኖ አልፏል። ኢትዮጵያ ከቀውስ ወደ ቀውስ እንድትሸጋገር ምክንያትም ሆኗል።እንደ መውጫበድምሩ፥ ምርጫ 97 የራሱ የሆኑ በረከቶችና መርገሞችን ይዞ መጥቷል።ከበረከቱ አንደኛው ሕዝቡ እድሉ ከተሰጠው፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ መሪዎችን ለመምረጥ ችሎታም ፍላጎትም እንዳለው ነው።ኢትዮጵያም ወደ ተስተካከለ ፖለቲካ ሽግግር ማድረግ እንደምትችል በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየበት ነው። አነሰም በዛ ፓርላማው ራሱ ከቀደመው በተወሰነ መጠን ልዩ መልክ እንዲኖረው፣ ክርክር የሚነሳበት እንዲሆን ያስቻለ የታሪክ ክስተት ነበር።ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን የቆዩ የፖለቲካ ልሂቃን አንድ ሆነው፣ ፍላጎቶቻቸውን አቻችለው የሀገርን አንድነትና ሕዝቦቿን ለመታደግ ያልበቁና ያልተሳካላቸው መሆኑ እንደ እርግማን የምቆጥረው ነው።በታሪክ ያመለጡንን እድሎች ከመጻፍ ውጭ እንዳንጠቀምባቸው ያደረጉንና በዋናነት የሚጠየቁት ወይም መጠየቅ ያለባቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው። ከኢሕአፓ እና መኢሶን ዘመን ጀምሮ ሕልሞቻችንን የማቻቻሉ ሁኔታ ላይ መዳከም፣ መደራደርና ሰጥቶ የመቀበል ፖለቲካ ውስጥ መግባት አለመቻል ዛሬ ለገባንበት ምስቅልቅል ዳርጎናል። ያለፉትን 20 ዓመታትም በዚያ ውስጥ ቆይተናል።ቀጣዩስ ምን ይሆን?ከ14 ዓመታት በፊት ባሳተምኩት መጽሐፌ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ ያልኳቸውን አራት ግምቶች እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያነቴም ጭምር ትንታኔዬን (scenario) አስቀምጬ ነበር። ይህ እንግዲህ ከ1997 ምርጫ ስድስት ዓመት በኋላ ነበር።የመጀመሪያው የወቅቱ ገዢ ፓርቲ ከሌሎች ፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሃቀኛ ውይይት አካሂዶ አዲስ ማኅበራዊ ውል ማሰር ከቻለ፣ አገሪቷ ተስፋ ሰጪ የሽግግር እድል ታገኛለች የሚል ነበር። ሁለተኛው የግምት ትንታኔዬ ገዢው ፓርቲ ተፎካካሪዎችን በማፈኑ ከቀጠለ ወደ ቀውስ እና ግጭት እንገባለን የሚል ነው።ሦስተኛው ደግሞ ፖለቲካው የመበስበስ እድል ይገጥመዋል የሚል ሲሆን አራተኛው ግን ኢትዮጵያ የመበታተን ዕጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል የሚል ነበር።አሁንም ቢሆን ግምቴ ከዚያ የራቀ አይደለም። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበትና መንገድ ችግሮቿ እየሰፉ፣ እየጠለቁ ሄዱ እንጂ እየተሻሻሉ እየተቀረፉ፣ ብሔራዊ መግባባት እየተፈጠረ፣ የተሳካ ዴሞራሲያው ሽግግር እያደረገች አይደለም።በመሆኑም የዛሬ 14 ዓመት ያስቀመጥኳቸው አደጋዎች አሁንም አሉ።ኢትዮጵያን በምናውቃት ደረጃ እንደሃገር የመፍረስ አሁንም ያለመቀጠል እድል ከፊታችን ተጋርጦ ይገኛል።በ2010 ሕዝቡ ለውጥ ሲያመጣ ፓርቲያችን ባይመዘገብለትም የራሱን አስተዋፅኦ አድርጎ ነበር። እኔን ጨምሮ በርካታ አባሎቻችን ከአስር የተፈቱት በለውጡ ነበር።ታዲያ ለ አንድ ዓመት አካባቢ የቆየው ይህ ለውጥ፥ ከ 1997 በማይተናነስ የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍቶ ነበር።ነገር ግን በተለይም ከሃጫሉ ግድያ ብሎም ካለፈው ምርጫ ወዲህ ምህዳሩ ከቀደመው በበለጠ ጠቧል።ያለፉት ሰባት ዓመታት ቀላል ያልሆነ የሕዝብ ደም የፈሰሰበት፥ ኢትዮጵያም አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ የገባችበት፥ ብዙ ነገሮች የተበላሹበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። እንደ ፓርቲም ዛሬ ላይ ከ 1997 እጅግ የጠበበ ምህዳር ውስጥ እንገኛለን።በተደጋጋሚ ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ብሎም እንደ ቁርአን ቃል መድገም የምፈልገው፥ ኢትዮጵያ ከአንድ ድርጅት፥ ፓርቲ ወይም ቡድን በላይ ናት። ይህንን ተረድተን ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ሃቀኛ ድርድር እናድርግ ስል ጥሪዬን እደግማለሁ። የመቻቻል ፖለቲካን ለማምጣት እንድንሠራ፥ ሃቀኛ ምርጫ ለማድረግ ከዛም ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን በጋራ ለመፍጠር - በተለይም ገዢው ፓርቲ ይሄንን ሰምቶ - ምናልባትም የመጨረሻውን ውለታ ለሕዝቡ ይውል ዘንድ ጥሪዬ ነው።
By Godana
ይህ የጽሁፍ አበርክቶ በምርጫ 1997 ወቅት የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ብሎም የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰብ ያበረከቱት ነው። ጸሃፊያችን ሃሳባቸውን እንጂ ማንነታቸውን እንድናጋራ ፈቃዳቸውን አልሰጡንም።የጥላሁን ገሰሰን “ከሰው ሰው ይለያል” የተሰኘውን ሙዚቃ ከጀርባ እያዳመጡ ፅሁፉን ያነቡ ዘንድ ፀሃፊያችን በጠየቁት መሰረት እኛም በግራ በኩል ባለችው ምልክት ላይ ሙዚቃውን አያይዘንዋል። ከ20 ዓመታት በፊት በግንቦት ሰባት ቀን 1997 ዓ.ም የተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የተከናወነበት ሂደት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስኬታማ የነበረ መሆኑን በርካታ ምርጫውን የታዘቡ እንደ የካርተር ሴንተር፤ የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ያሉ ተቋማት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በምርጫው ተቃዋሚ ድርጅቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ የተሳተፉ ሲሆን፣ በፓርላማ ውስጥ ያላቸውን መቀመጫ ከማሳደጋቸውም በላይ (ከ12 ወደ 170 ወንበር) የአዲስ አበባ ምርጫን ሙሉ ለሙሉ አሸንፈዋል። የሆነ ሆኖ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ጥርጣሬ በኅብረተሰቡ ውስጥ ውጥረት እንዲሰፍን ተደርጎ በሰኔ ወር 1997 ከፍተኛ አመጽ ተቀሰቀሰ። ለዴሞክራሲ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ የተጣለበት የምርጫ ሂደት በሚያስቆጭ ሁኔታ ተጨናገፈ።በዚህ አጭር ጽሑፍ ተስፋ ተጥሎበት ስለነበረው ምርጫ 97 እና የወቅቱ ድባብ፤ የምርጫውን ሂደትና ፈንጥቆ ስለነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል መዳፈን ለመግለጽ እሞክራለሁ።የወቅቱ የምርጫ ሂደትበበርካታ ሀገራት የሚካሄዱ ምርጫዎች በሦስት ምዕራፎች ያልፋሉ። በመጀመሪያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የራሳቸውን ዝግጅት አድርገው ፕሮግራማቸውን በማስተዋወቅና ሕዝብ ውስጥ በመንቀሳቀስ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት እንዲሁም እርስ በእርሳቸው ክርክር የሚያደርጉበት ነው። ሁለተኛው ምዕራፍ ድምጽ የሚሰጥበት፤ ቆጠራ የሚካሄድበትና ውጤት የሚገለጽበት ምዕራፍ ሲሆን፣ ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ በድምጽ ቆጠራው መሰረት አሸናፊ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች በውጤቱ መሰረት መንግሥት ለመመስረት የሚረከቡበት ነው።የምርጫ ዝግጅትና ቅስቀሳ“ምርጫ 97 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ካካሄዳችው ሁለት ምርጫዎች (1987 እና 1992) ለምን የተለየ ሆነ?” የሚለውን ጥያቄ ልዳስ። ይህን ጥያቄ ማንሳቱና ማብራራቱ ምናልባትም በምርጫ 97 ወቅት የነበረውን ኹኔታ ለመገንዘብ ይጠቅማል ብዬ አምናለኹ።እንዲኸ ነው፡- በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ሀገሪቱን ባስተዳደረበት የመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት (1983 እስከ 1993 ዓ.ም) የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተዋሉ ነበር። ከዚያም ባሻገር የኤርትራ መንግሥት ወረራን ለመመከት የተካሄደው ጦርነት እንዲሁም 14 ሚሊዮን ሕዝብን ለአደጋ ያጋለጠው ድርቅ መንግሥትን ከፍተኛ ችግር ውስጥ አስገብቶት ነበር። በዚህም የተነሳ በኅብረተሰቡ ውስጥ በተለይም በከተሞች ብሶትና ተስፋ መቁረጥ የተስፋፋበት ግዜ ነበር።ኢሕአዴግ፥ እነዚህን ችግሮች በቶሎ ለመፍታትና ልማትን ለማሳለጥ የትጥቅ ትግል በሚያካሂድበት ወቅት ይከተለው የነበረውን የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን ተወ። እናም የካፒታሊስት ስርዐት የሚገነባ መሆኑን በመግለጽ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ንድፈ ሐሳብን መሰረት ያደረጉ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። በዚህ ወቅት አዳዲሶቹን ፖሊሲዎች ለመተግበር ከፍተኛ መከራ የገጠመው ቢሆንም፣ ችግሮችን በመፍታት ልማትን ለማሳለጥ ሌት ከቀን መሥራት ጀመረ። በምርጫ 97 ዝግጅት ወቅትና ምርጫው በሚካሄድበት ጊዜም በሀገሪቱ (በገጠርም ሆነ በከተማ) እዚህ ግባ የሚባል የሕዝብን ኑሮ የለወጠ ልማት አልነበረም። ለምሳሌ በገጠር በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጥ የታየ ሲሆን በከተሞች በተለይ በአዲስ አባባ ደግሞ የአነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች፤ የቤቶች ልማት እንደዚሁም ሰፋፊ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች የተጀመሩበት ጊዜ ነበር።ይህ በእንዲህ እያለ፣ ኢሕአዴግ ምርጫ የሕዝብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ በመሆኑ በ1997 የሚካሄደው ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ መሆን ይገባዋል የሚል አቋም ይዞ ተንቀሳቀሰ። ድርጅቱ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የሕዝብን መብት ለማክበር የቆመ ድርጅት በመሆኑም፣ ይህ አቋም ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ1983 ዓ.ም ደርግን አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን ሲይዝ፣ ለብቻው ሳይሆን በርካታ ድርጅቶችን አሳትፎ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሲደረግ ነበር።በመሰረቱ አንድ ሕዝብ በምርጫ ተጠቃሚ የሚሆነውና ሉዐላዊነቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማረጋገጥ የሚችለው የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለት ይበጀኛል ያለውን በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው። በሕገ-መንግሥቱ ላይ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብቶች እንደሚከበሩ ተደንግጓል፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት በመገንዘብ ወደ ምርጫ ውድድር የገባው፥ ቢሸነፍም ውጤቱን በጸጋ መቀበል የዴሞክራሲ መርህ መሆኑን በመገንዘብም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ተቃዋሚዎች በብዙኀን መገናኛ ሰፊ እድል እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲ ምርጫ ማስፈጸሚያ መንገድ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር የፖሊሲ ክርክር እንዲካሄድ አደረገ። ክርክሩም ምርጫው ከመካሄዱ ከ9 ወር በፊት (ከመስከረም 1997) ጀምሮ ተካሄደ። ከዚህም በላይ የምርጫ ሕጉ እንዲሻሻል ተቃዋሚ ድርጅት የሆነው አዴፖ/መድሕን ያቀረበውን ጥያቄ በመመርመር የምርጫ ሥርዓቱ ከአብላጫ ድምጽ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲቀየር ከተጠየቀው በስተቀር ለአብዛኞቹ ጥያቄዎች ይሁንታን ሰጠ። በተጨማሪም ኢሕአዴግ የምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ጥረት ያደረገው ተቃዋሚዎች መድረክ አጣን በሚል ምክንያት ሊያስነሱ የሚችሉትን ሕዝባዊ አመጽ ለመግታት ነበር፡፡የኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች የምርጫ ክርክርእንደ ኢሕአዴግ ሁሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም በምርጫው ለመሳተፍ የተለያዩ ዝግጅቶችን አድርገዋል። ለምሳሌ “ስንበታተን የምርጫ ድምጹም ይከፋፈላል” በሚል እሳቤ ብዙዎቹ አንድነትን ፈጥረው ተንቀሳቅሰውም ነበር። በዚህም መሰረት በራሳቸው በተቃዋሚዎች በመካከል ብሎም ከኢሕአዴግ ለዘጠኝ ወራት የዘለቀ ሰፊ እና የተጋጋለ ክርክር ለመካሄድ በቃ። ሕዝቡም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክርክሮቹን በመከታተል የሚስማማውን ለመምረጥ ዕድል አገኝቶ ነበር።የፖለቲካ ክርክሩን መድረክ ያዘጋጁት በዋናነት እንደ ኢንተር-አፍሪካ የመሳሰሉ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተካሄዱ ክርክሮችም ነበሩ። ለክርክሮቹ መነሻም በኢሕአዴግ በኩል ፖሊሲዎቹ የሆኑት የመሰረተ ልማት፣ የገጠር፣ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት፣ የመሬት ፖሊሲ፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ፋይዳ፣ ስለፌዴራሊዝምና የብሔር እኩልነት ወዘተ ናቸው። ብዙዎቹ ኢሕአዴግን በመወከል የተሳተፉ ተከራካሪዎች አቀራረባቸው በተገቢው ሁኔታ ያልተዘጋጁ በሚመስል መልኩ ነበር። ይህን ሁኔታ የታዘቡት አንዳንድ ግለሰቦች ስለሁኔታው ሲገልጹ “ኢሕአዴግ በባህሪው ሠርቶ በማሳየት እንጂ ስለሥራው ብዙም የሚናገር አይደለም” ይሉ ነበር፡፡ እውነትም በድርጅቱ ‘ሥራችን ይናገራል፣ እኛ ስለሥራችን ብዙም መናገር የለብንም’ የሚለው አስተሳሰብ በየጊዜው የሚንጸባረቅ መሆኑን እኔም እገንዘባለሁ። በጊዜው ኢኮኖሚው ከውድቀት ተነስቶ ማንሰራራት መጀመሩም ሆነ አስተማማኝ ሰላም ስለመኖሩ በምርጫው ክርክሮች በግልጽ አልቀረበም፡፡ ከምርጫው ሁለት ዓመት በፊት የተገኙትን መልካም ውጤቶች እንኳን በጥልቀት ለማስረዳት በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ ከማቅረብ ይልቅ ጥልቀት በሌለው ሁኔታ ሥራዎቹን አስተዋወቀ፡፡ በተቃዋሚዎችም በኩል ምርጫ ቢያሸንፉና የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙ ስለሚከተሉት የልማት አቅጣጫ እዚህ ግባ የሚባል ፖሊሲና ስትራቴጂ አልቀረበም፡፡ከዚህም በላይ ተቃዋሚዎች የመንግሥት ፖሊሲዎችን እያጥላሉ የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት ይጥሩ ነበር። ለምሳሌ ከላይ እንደገለጥኹት፥ በከተሞች ኢሕአዴግ የልማት ሥራዎችን የጀመረው ዘግይቶ ስለነበር በርካታ ሥራ አጦች ነበሩ። ተቃዋሚ ድርጅቶችም የሥራ አጦችን ብሶት ማራገብ ከመጀመራቸውም በላይ፣ ለበርካታ ሚሊዮን ሕዝቦች የትምህርት እድል የፈጠረላቸውን ትምህርት ማጥላላትን ተያያዙት። ተማሪዎችንም ተስፋ ለማስቆረጥ ‘ተምራችሁ የት ትደርሳላችኹ’ የሚል ዘመቻ አካሄዱ። በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ትምህርት “ትውልድ ገዳይ ነው” በሚል ከመፈረጃቸውም በላይ፥ “ተምረኽ የት ትደርሳለኽ!“ “የተቸገረ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” የሚሉ ከባባድ መልእክቶችን በመጠቀም ወጣቱ ‘ተምረን የት ልንደርስ?!’ በሚል ተስፋ ማስቆረጥን ተያያዙት።በተጨማሪም የሕዝብን ብሶት በማባባስ ለማሳመጽ የባለሥልጣናትን ስም እያነሱ ‘እገሌ ይሄን ያህል ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውጭ አስቀምጧል/ እገሊትም ይህን ያህል ፓውንድ አስቀምጣለች’ በሚል የፈጠራ ወሬ ወጣቱን የአመጽ መሣሪያ እንዲሆን ገፋፉት። ኢሕአዴግም የተቃዋሚዎቹን አፍራሽ ቅስቀሳ ተከታትሎ በአግባቡ ከማክሸፍ ይልቅ ተቃዋሚዎች በከተሞች የተንሰራፋውን ሥራ አጥ ኃይል ተጠቅመው ወደ ሥልጣን ለመምጣት እየተረባረቡ ነው በሚል እሳቤ፥ ሥራ አጥ ወጣቶችን “አደገኛ ቦዘኔ” በማለት የተቃዋሚዎቹ ማኅበራዊ መሰረት ናቸው የሚል አንድምታ አስተላለፈ። “አደገኛ ቦዘኔ” የሚለው አጠራር በመሰረቱ ትክክል አልነበረም። ምክንያቱም ወጣቶቹ ሥራ አጦች እንጂ ሥራ ጠል አልነበሩምና። ይህ አባባልም ወጣቶቹ መንግሥት “አደገኛ ቦዘኔ” ብሎ ሊያጠፋን ነው ብለው በማሰብ ወደ ተቃዋሚዎች አስተሳስብ እንዲያዘነብሉና በሥርዓቱ ላይ የማመጽን አስፈላጊነት እንዲቀበሉ ያደረገ ይመስለኛል፡፡የምረጡኝ ቅስቀሳየምርጫ ቅስቀሳው የተካሄደው በሚዲያ በሚተላለፉ መልዕክቶች ብቻ አልነበረም። የኢሕአዴግ ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች በየምርጫ ክልላቸውና ወረዳቸው እየተገኙ የምረጡኝ ቅስቀሳ ከማከናወናቸውም በላይ፥ ከተቃዋሚዎችም ጋር በየጣቢያው የምርጫ ክርክር ያደርጉ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች (በተለምዶ ፒክ አፕ፣ አይሱዙ ተብለው በሚጠሩት) እየተጫኑና የድምጽ ማጉሊያ በመጠቀም፤ አልፎም ትልልቅ ሰላማዊ ሰልፎች በማካሄድ በተለይም በከተሞች የምረጡኝ ቅስቅሳ ይካሄድ ነበር። ሕዝቡም በሬድዮና ቴሌቭዥን የሚካሂዱትን ክርክሮች ያደምጥና ይመለከት፣ አልፎም በወቅቱ እንደአሽን ፈልተው የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚያወጧቸውን ጽሑፎች ይከታተል ነበር።አንዳንድ ጊዜ ከአዲስ አባባ ውጭ በመኪና ስንሄድ ትንንሽ ልጆች በየመንገዱ ቆመው የቅንጅትን የምርጫ መወዳደሪያ ሁለት ጣት (V) ምልክት በትንንሽ ጣቶቻቸው እያወጡ ያሳዩን ነበር። የ97 ምርጫ የፓለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን የመላ ሕዝቡን (በገጠርም በከተማም የሚገኘውን) ቀልብ የሳበ ነበር። ለዚህም ማስረጃ በሚያዝያ ወር የመጨረሻው ቅዳሜ በኢሕአዴግ፥ እንዲሁም በማግስቱ እሁድ በቅንጅት የተካሄዱትን መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎችን መጥቀስ ይቻላል።የድምጽ መስጠትና ውጤትበምርጫው ዕለት ግንቦት 7 በመላው ኢትዮጵያ ሕዝቡ በሌሊት ተነስቶ እስከ ማታ ድረስ ድምጽ ሰጠ። የድምጽ አሰጣጡ ሂደት በጣም ሰላማዊ ሆኖ አለፈ። የሆኖ ሆኖ የምርጫ ሂደቱ ገና ሳይጠናቀቅና ቆጠራ ሳይካሄድ የመኢአድ ፓርቲ መሪ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል በሚያስገርም ሁኔታ ፓርቲያቸው ምርጫውን እንዳሸነፈና ኢሕአዴግም ምርጫውን እንዳጭበረበረ መግለጫ ሰጡ።የድምጽ መስጠት ሂደቱ እንደተጠናቀቀም፣ በወቅቱ የነበሩት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ገለጹ። አያይዘውም፥ የተፈጠረው ውጥረት እንዲበርድ፣ መራጩም የምርጫውን ውጤት በጥሞና እንዲጠብቅና እንዲቀበል እንዲሁም ግጭትን ለማስቀረት በማሰብ መንግሥት ለአንድ ወር ለሚሆን ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ እንደከለከለ አስታወቁ።የድምጽ ቆጠራው እንዳለቀ በውጤቱ፥ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ እንደተሸነፈ፣ በፌዴራል ደረጃ በርከት ያሉ ወንበሮችን ያጣ ቢሆንም ለፓርላማው ግን አብላጫውን ድምጽ መያዙ ተገለጸ። ተቃዋሚዎች ደግሞ በ1992 ከነበራቸው 12 የፓርላማ ወንበር በ97 ምርጫ ወደ 170 ወንበር አሳደጉ። የሆነ ሆኖ ተቃዋሚዎች ሙሉ በሙሉ ምርጫውን ባለማሸነፋቸው የምርጫውን ውጤት ላለመቀበል ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል መነሻ አመጽ ማነሳሳት ጀመሩ።አመጽ የማነሳሳት ድርጊቶችቅንጅቶች መሸነፋቸውን ባለመቀበልና በማንኛውም መንገድ ሥልጣን መያዝ ይገባናል በሚል ብሂል፥ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ሰበብ በተከታታይ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት አመጽ የመቀስቀስ እንቅስቃሴ ጀመሩ። በሀገሪቱ ምርጫ ሕግ በምርጫ ውጤቱ ያልተስማማ ወገን በመጀመሪያ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄዶ እንዲያመለክት፤ በምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ካልተስማማ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ተቀምጧል። አንድ ዴሞክራሲንና ሕግን የሚያከብር ድርጅት ይህንን ሕጋዊ መንገድ የሚከተል ቢሆንም፤ የቅንጅት አመራር ግን አግባብ ያለውን መንገድ መከተል አልፈለገም። ምክንያታቸውም ምርጫ ቦርዱም ሆነ ፍርድ ቤቱ ለኢሕአዴግ ያዳላል የሚል ነበር።በዚህም ምክንያት የጎዳና አመጽ ተቀስቅሶ ግርግሩ ሲባባስ ፖሊስ አድመኛውን ለመበተን ብሎ በተኮሰው ጥይት የአንዲት ወጣት ሕይወት በሚያሳዝንና ባልተገባ ሁኔታ አለፈ። ይህ በመሆኑ በመጸጸትና ሌላ ሕይወት እንዳይጠፋ ሁኔታውን የሚያበርድ እርምጃ በመውሰድ ፈንታ፣ የቅንጅቱ አመራሮች የወጣቷን ሞት ለጎዳና ነውጥ እንደማቀጣጠያ ቤንዚን ተጠቀሙበት። በመሆኑም የጎዳና ነውጡ የመንግሥት ንብረት በማውደም፤ አንበሳ አውቶብስን በድንጋይ በመደብደብ፤ የመንግሥትና የግል ተሽከርካሪዎችን በማቃጠል፤ በየመንገዱ አሮጌ ጎማዎችን በማቃጠልና መንገድ ላይ ድንጋይ እየከመሩ መንገዶችን በመዝጋት ተቀጣጠለ፡፡ፖሊስም እንደ ማርያም ጠላት ተወስዶ የድንጋይ ናዳ ወረደበት፤ ጥይት ተተኮሰበት። ለምሳሌ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ ጸጥታ ለማስከበር በኦራል ተጭነው ሲሄዱ በነበሩ ፖሊሶች ላይ ቦንብ ተወርውሮባቸው ጥቂቶቹ ሲሞቱ በርካታዎቹ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባችው ነበር፡፡ ፖሊሶችም አድማውን ለመበተንና ሁኔታውን ለማረጋጋት በተኮሱት ጥይት በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ። የሆነ ሆኖ ግርግሩ በሦስተኛው ቀን (ሰኔ 3) ሰከነ።በተቃዋሚዎች “እኛ ሁሉንም ጠቅልለን ካላሸነፍን ምርጫው ዴሞክራሲያዊ አይደለም” የሚል ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት የተነሳ በርካታ ወጣቶች ያለአግባብ ሕይወታችው ጠፋ። ወላጆችንም ጧሪ ቀባሪ አሳጧቸው፡፡ እዚህ ላይ ‘ኢሕአዴግስ ለምን ወደ ጥይት ሮጠ?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፤ መነሳቱም ተገቢ ይመስለኛል።በመሰረቱ ኢሕአዴግ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የወሰዳቸውን እርምጃዎችና ብሎም ሽንፈት ቢመጣ እንኳን ሥልጣኑ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን ከላይ ገልጫለኹ፡፡ የሆነ ሆኖ ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት በጸጋ ባይቀበሉት እንኳ፣ ከላይ በገለጽኩት ደረጃ የመንገድ አመጽ ያስነሱ ይሆናል በሚል ዝግጅት በማድረግ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገው ኢሕአዴግም ይህንኑ ተጠቅሞ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ነበረበት (እኔም ተማሪ ሆኜ በንጉሡ ዘመን ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ስንረብሽ አብዛኛውን ጊዜ የሚበትኑን በአስለቃሽ ጢስና በፖሊስ ቆመጥ ነበር)። የሰኔው የጎዳና ነውጥ እንዳይደገም የምርጫ ውዝግብ የሚፈታበትን መንገድ አና ስልት በዓለም አቀፍ የምርጫ አማካሪ ድርጅት በኩል እንዲዘጋጅ ተደረገ። ኢሕአዴግ የምርጫ ሂደቱን አስመልክቶ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታዎች ለማስተናገድ ስልቱን ለሁሉም ፓርቲዎች በማቅረብ ሁሉም የተስማሙበት የቅሬታ አፈታት ስልት ተዋቀረ። የተመሰረተው ስልትም ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥሩ መንገድ እንደነበር የምርጫ ታዛቢዎች፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የመሰከሩለት ነበር፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የችግር መፍቻ መንገድ በወቅቱ በነበረው ውጥረት ውስጥ ሊሠራ ስለማይችል፣ አዲስና ሁሉም ፓርቲዎች የተስማሙበት አሰራር ተዘጋጀ፡፡ በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎች በሰጡት የጽሑፍ ሪፖርት (በሪፖርቱ ገጽ 4 እና 5 ላይ ይገኛል) ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ቅሬታዎች በደካማ ማስረጃ (poor evidence) የተገለባበጠ ምስክርነትና ደካማ መከራከሪያ (week argument) ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።በተቃራኒው ግን አብዛኛው ኢሕአዴግ ያቀረባቸው ቅሬታዎች በማስረጃ የተደገፉ ከመሆናቸውም በላይ ወኪሎቻቸውና ምስክሮቻቸው በደንብ የተዘጋጁ እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በመሆኑም ድርጅቱ አብዛኛውን ቅሬታ ያቀረበበትን ማሸነፉ እንደማያስደንቅ አስታውቋል።ለማጠቃለል፥ የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎች ከዚህ የሚከተሉትን 4 ነጥቦች አስቀምጠዋል።የቅሬታ ሰሚ ሜካኒዝሙ ለነበረው ውጥረት ያየለበት ሁኔታ ጥሩ እንደነበር፣የቅሬታ አገማገሙም የተቀመጠውን ሂደት (ፕሮሲጀር) የተከተለ እንደነበር፣ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለቅሬታዎቻቸው ጠቃሚ ማስረጃ (Substantial evidence) ለማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን ምስክሮቻቸው የማይጣጣሙ (Inconsistent) እንደነበሩ፣ኢሕአዴግ ግን ጉዳዩን (Case) በደንብ ማቅረቡና መከራከሩ።በተጨማሪም የድርጅቱ አጠቃላይ ግምገማ የምርጫ ሂደቱ (polling process) አወንታዊ (positive) ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለግምገማቸው የሰጡት ነጥብ 64% የሚሆኑት ጉዳዮች (cases) ጥሩ ናቸው ሲሉ፥ 24% ደግም በጣም ጥሩ በሚል አስቀምጠዋል፡፡ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ አሸናፊ በተባለበት በርካታ የምርጫ ጣቢያ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ቅሬታ አቀረቡ፡፡ ኢሕአዴግም እንደዚሁ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ቅሬታ አቀረበ፤ ቅሬታ የቀረበባቸው ጉዳዮች ከተመረመሩ በኋላ በ31 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ ከፍተኛ ክፍተቶች (serious irregularities) መኖሩ ታወቀ። ከቀረቡት 31 ቅሬታዎች 17 በኢሕአዴግ፣ 7 በተቃዋሚዎች፣ 4 በኢሕአዴግና በአንዱ ወይም በሌላው ተቃዋሚ ድርጅት ጋር ቅንጅትንም ጨምሮ በጋራ የቀረበበት ነው። ቀሪው 3 ደግሞ በምርጫ ቦርድ ውጤቶች ያልተወሰና ዳግም ነበሩ።ቅሬታዎቹ ከተመረመሩ በኋላ ኢሕአዴግ ያቀረባቸውን 17 ቅሬታዎች ሲያሸንፍ፣ ተቃዋሚዎች ያቀረቧቸው 7 ቅሬታዎችን በሚመለከት ደግሞ ኢሕአዴግ ተሸንፏል። 4ቱ በጋራ የቀረቡት ቅሬታዎችም በጋራ ያቀረቡት ድርጅቶች እንደዚሁ አሸንፈዋል።ዳግም ምርጫ የተካሄዱባቸው ጣቢያዎች ከ29 ሺህ 438 ውስጥ 575 ሲሆኑ፣ ከመቶ ሲሰላ ከሁለት በመቶ (2%) ያነሱ ነበሩ። የምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳየውም አብዛኛዎቹ ጥፋተኞች (culprit) ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢሆኑም ኢሕአዴግም ከደሙ ንጹህ አልነበረም። የዳግም የጎዳና ነውጥ መከሰትከላይ እንዳነሳኹት፥ የምርጫ ሂደቱን የማጣራትና ቅሬታን የማስተናገድ ሂደት በፓርቲዎች ስምምነት መሠረት ተካሂዷል። በተጨማሪም አመጹን ለማስቀረት መንግሥት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም ከቅንጅትና ኅብረት አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይትና ድርድር አካሂዷል። ሆኖም የጎዳና ላይ ነውጥን ማስቀረት አልተቻለም።ቅንጅት የተጣራውን የምርጫ ውጤትና ያሸነፈውን መቀመጫ በመያዝ ወደ ፓርላማ እንደመግባት ፋንታ፣ በየክፍለ ከተማው የመረጠውን ሕዝብ እየሰበሰበ “ወደ ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ?” የሚል አስቂኝ ጥያቄ በማንሳት “ፍቃድ” ጠየቀ። በመጨረሻም በአመጽ ሥልጣን ለመያዝ የሚያልሙት መሪዎች ሁሉንም መቀመጫ ካላሸነፍን በሚል ስሜት ሁለተኛውን የጎዳና ላይ ነውጥ በጥቅምት ወር 1998 ውስጥ ቀሰቀሱ። እንደ መጀመሪያው ሁሉ በድጋሚ ክቡር የሆነው የፖሊሶችና ጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ በርካታ የሰው ሕይወት ጠፋ፣ ንብረትም ወደመ። ነውጡ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን መንግሥት ለነውጡ ቅድሚያ የሚሰጡት የቅንጅት መሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ወሰነ። በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ሕብረት እና ኦፌዲን እንዲሁም ኢዴፓ (ከቅንጅት ራሱን በመነጠል) ፓርላማ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን በማለት አቋማቸውን አሳወቁ።በነገራችን ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እነ ኢዴፖ ወደ ፓርላማ መግባታቸው ለፓርላማው ሕይወት ሰጥቶት ነበር። ምክንያቱም በፓርላማ ውስጥ ለውሳኔ የሚቀርቡ ጉዳዮች ሁሉ በለሆሳስ የሚያልፉበት ተቋም መሆኑ ቀርቶ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር የሚካሄድበት መድረክ ሆነ። በተለይም ጠቀላይ ሚኒስትር መለስ በየሁለት ወሩ ወደ ፓርላማው መጥተው የአባላቱን ጥያቄ በሚመልሱበት ወቅት የሚካሄዱት ውይይቶችና ክርክሮች በጣም አስተማሪ ነበሩ።የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሂደት ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲ የሚነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች እንዲሁም የሚሰጡ መልሶች አስተማሪ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዴም አስቂኝ ስለነበሩ፥ እኔና ጓደኞቼ ወቅቶቹን በጉጉት እንከታተላቸው ነበር።የኔ ድምዳሜብዙውን ጊዜ በሀገራችን ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች በአንድ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ወይም ሲከራከሩ ላለመሸናነፍና ሁሌም በኔ መንገድ መሆን አለበት በሚል ግትር አስተሳሰብ በመያዝ ልዩነቶችን ተቀብሎ፣ በሚያስማሙ ሐሳቦች አብሮ ለመሥራት ባለመፈለግ በርካታ ስህተቶች ይፈጸማሉ። በ97 ምርጫ የተሳተፉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን አመለካከት በመከተል በወቅቱ ያገኙትን ድምጽ በመጠቀም (በፊት ከነበራችው 12 የፓርላማ መቀመጫ ወደ 170 አሳድገዋል፤ ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ አሸንፏል) በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መሥራት ነበረባቸው። በአንጻሩ እነርሱ ሁሉንም ካላሸነፍን በማለት አመጽ በማስነሳት ያለአግባብ የበርካታ ሰው ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኑ። ይህንን ሁኔታ ሳስታውስ፥ በደርግ ጊዜ የተካሄደውን በሁለት ግራ ዘመም ርዕዮተ አለም (አይዲዎሎጂ) በሚከተሉ ድርጅቶች (ኢሕአፓ እና መኢሶን) መካካል በተፈጠረውና በውይይት ሊፈታ ይችል በነበረው የሐሳብ ልዩነት ምክንያት የፈሰሰው ደም ብሎም ሊገነባ ይችል የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት መጨናገፉን አስባለኹ።እንደዚሁ ሁሉ የምርጫ 97 መጨናገፍም ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲ የመራመድን ተስፋ ያጨለመ ነበር። ምክንያቱም የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ የሆነው የሕዝቦች ፍላጎት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ አለመረጋገጡ የዴሞክራሲ ጅምሩ ማኮላሸቱን ያሳያል። 97 ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በተካሄደው 2002 ምርጫ 63 ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረው ከሁለት የፓርላማ ወንበሮች በስተቀር ሁሉንም ኢሕአዴግና አጋሮቹ አሸነፉ። ይህ ሁኔታ ለምን እንደተፈጠረ ቢጠና ጥሩ ትምህርት የሚሆነን ቢሆንም፥ ምናልባትም የምርጫ 97 አሉታዊ አስተዋጽኦ ይኖርበት ይሆን የሚል ሐሳብም ያጭርብኛል።ተስፋ አደርጋለኹ፥ ወደፊት በሀገራችን ማንኛውንም ልዩነቶች በውይይትና ሰጥቶ በመቀበል እሳቤ የማካሄድ ባህል ጎልብቶ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓትም ተመስርቶ ሕዝቦች በመረጡት መንገድ እንደሚተዳደሩ። ደግሞም ምክር ቤቶቻችን የሕዝብን ጥያቄ አንስተው የሚከራከሩበት እንጂ የጎማ ማህተም (rubber stamp) የማይሆኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠር፥ ተስፋ አደርጋለኹ።